Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኮሮና ወረርሽኝ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 28፣ 2012( ኤፍ.ቢ.ሲ)በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር ለሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ አድርገዋል።

የኮሮና ወርርሽኝ ጫና ካሳደረባቸው ዘርፎች አንዱ በተለያየ ምክንያት ችግር የደረሰባቸው ሰዎችን የሚደግፉ የበጎ አድራጎት ተቋማት መሆናቸው ተገልጿል።

ከነዚህ ውስጥ ከተመሰረተ ከ20 አመት በላይ የሆነውና ከአንድ ሺህ በላይ ህጻናትና እናቶችን የሚያስተዳድረው ሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር አንዱ ነው።

በወረርሽኙ ምክንያት ድርጅቱን የሚጎበኙና የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር በመቀነሱ የሚያስተዳድራቸውን ሰዎች ለመመገብ ተቸግሮ እንደነበር የማህበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ ተናግረዋል።

ችግሩን ለፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በማሳወቃቸው ፕሬዝዳንቷ በጎ ፈቃደኞችን አስተባብረው ምላሽ እንደሰጧቸውም ነው የሚናገሩት።

ፕሬዝዳንቷ የተለያዩ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ከ660 ሺህ ብር በላይ በማሰባሰብ ለሁለት ወር የሚሆን የምግብ ወጪ ሙሉ ለሙሉ መሸፈናቸውን ተናግረዋል።

በማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ታደለ አየለ በበኩላቸው÷ በማህበሩ ውስጥ ድጋፍ የሚደረግላቸው ህጻናት የሚማሩት የመንግስት ትምህርት በመሆኑ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ቁርስና ምሳ ትምህርት ቤት ይጠቀሙ እንደነበር ገልጸዋል።

በወረርሽኙ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው የምግብ አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ በማህበሩ ለመሸፈን በመቸገሩ የመዘጋት አደጋ ገጥሞትም ነበር ነው ያሉት።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር ያደረጉት አስተዋጽኦ ማህበሩን ከመዘጋት መታደጉን በመግለጽ ማመስገናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version