Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲሱ የመደመር መንግሥትና ፓርላማው …

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥት ምሥረታ አዲስ የአመራር ምዕራፍን ይከፍታል፡፡ አዲሱ አመራር በሥራ አፈጻጸሙና በሚያስመዘገበው ውጤት በህዝብ ዘንድ እውቅናም ይሁን ወቀሳ የሚታወስ ይሆናል።
ኢትዮጵያም አዲሱን መንግሥት መሥርታና ካቢኔውን አዋቅራ ወደ አዲስ የሥራ ምዕራፍ ገብታለች።
በዛሬው የሚኒስትሮች ሹመት የብሔር፣ የኃይማኖት፣ የጾታ፣ የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ልምድ፣ የማስፈጸም አቅምና ሌሎችን መስፈርቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድጋሚ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መሰየም እና ዛሬ የተደረገው አዲሱ የሚኒስትሮች ካቢኔ ሹመት የአዲሱ መንግሥት ሥራ ወደ አዲስ የአፈጻጸም ዘመን መሸጋገሩን ያመላክታል።
አዲሱ ካቢኔ የቀጣዮቹን የአምስት ዓመት የሥራ አቅጣጫ ለማስፈጸም የአመራር አቅምን ያደራጃል።
የተጀመሩ ሥራዎችን በማስቀጠል፣ ክፍተቶችን መሙላትና አዳዲስ ግቦችን ወደ ተግባር ማውረድ ዋና ተግባሩ ይሆናል።
በዚህ ሂደት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ወሳኝ ሚና አለው። ሕግ ከማውጣት ባለፈ የመንግሥትን አፈጻጸም መከታተል፣ የሕዝብን ጥያቄ ማስተጋባትና ተጠያቂነትን ማጠናከር ከዋና ተግባራቱ ውስጥ ይጠቀሳሉ።
የፖለቲካ ትብብርና ፉክክር በተቋማዊ መንገድ መመራቱም ለዚህ ሂደት ወሳኝ ነው፡፡
መንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑ የተለያዩ ሐሳቦች በውይይትና በሕጋዊ ሂደት የሚቀርቡበትን ምኅዳር ያሰፋል። ይህ ከሀገራዊ ምክክሩ ምክረ ሐሳቦች ጋርም የተጣጣመ አካሄድ ነው።
ከምክክሩ የሚመነጩ ሐሳቦችን ወደ ሕግና ተቋማዊ አፈጻጸም ማሸጋገር በቀጣይ የሚጠበቅ ትኩረት ነው።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በመንግሥት ምስረታው ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ርዕይ በሚያስብ አእምሮና በሚሠሩ እጆች ሲመራ እንደሚሰምር ገልጸዋል። ይህም ርዕይ ዋጋ የሚኖረው በተግባር ሲተረጎም መሆኑን የሚያመላክት ነው።
በዚህ መልኩ መንግሥት ያስፈጽማል፤ ፓርላማው ይቆጣጠራል፤ የሕዝብ ጥያቄም ወደ ሕግ፣ ፖሊሲና ተግባር ይተላለፋል። የሁለቱ ተቋማት ሚና በተገቢው ሲወጣ የሥራ ውጤታማነትና ተጠያቂነት ይጠናከራል።
#የመደመር_መንግሥት
በአመለወርቅ ደምሰው

Exit mobile version