Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሥልጣን ኮፍያ እንጂ…

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)በሥልጣንና በኮፍያ መካከል ያለው ዘይቤያዊና ፍልስፍናዊ ትሥሥር እጅግ የጠለቀ ነው። ኮፍያ ፀሐይ ወይም ከቅዝቃዜ በበረታ ጊዜ ይደፋል፤ አስፈላጊ ካልሆነ ደግሞ ተወልቆ ይጣላል ።
ሥልጣንም እንዲሁ ነው። ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት ብቻ የሚውል መሣሪያ እንጂ የማንነት አካል ወይም ከአካል የማይነጠል ጭንቅላት አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲሱን የመደመር መንግሥት የካቢኔ አባላት ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፥ “ሥልጣን ኮፊያ እንጂ ጭንቅላት አይደለም፤ በማንኛውም ሰዓት ፀሐይ ካልበረታ ወይም አስፈላጊ ካልሆነ ሊነሣ፣ በክብር ሊቀመጥ ወይም ተሽቀንጥሮ ሊጣል የሚችል ነገር ነው” ሲሉ ያስረዱትም ይህንኑ ፍልስፍናዊ እውነት የሚገልጥ ነው።
ዘይቤአዊ ማብራሪያው የሚያሳየን፥ ሥልጣን ጊዜያዊና ለሀገር እና ለሕዝብ አገልግሎት ብቻ የሚጠቅም መሆኑን ሲሆን፣ ተሿሚዎች በሥልጣን ሳይመኩ ማንነታቸውን ከወንበራቸው ለይተው ማየት እንዳለባቸውና ተጨባጭ ውጤት ባላሰገኙበት ወቅት በማንኛውም ሰዓት ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል ያስገነዝባል።
ይህ ንግግር፤ ትናንት ለተሾሙት የካቢኔ አባላት ብቻ ሳይሆን ለ54 ሚሊየን መራጮች የሚያስተላለፈው ትልቅ መልዕክት አለው። የመደመር መንግሥት የተሰጠውን የሕዝብ ድምጽ ከማከበርም በላይ፤ የትልቅ ሀገርንና የትልቅ ሕዝብን መሻት ለመፈጸም ምን ያህል ቁርጠኛ መሆኑን ያስገነዝባል።
የጥንታዊት ቻይና ፈላስፋ ላኦ ዙ÷ ከሁሉ የላቀው የመሪ ዓይነት የሚሠራው ለታይታ አይደለም፤መሪዎች የሥልጣን ትዕቢትን አውልቀው በመጣል፣ የታየውን ስኬት ከሕዝብ ጋር በመጋራት እውነተኛውን የአገልጋይነትና የትሕትና ጥግ ማሳየት እንዳለባቸው ያስረዳሉ።
በተመሳሳይ ታላቁ አፍሪካዊ መሪ ኔልሰን ማንዴላ÷ “ተግባር የሌለው ርዕይ ሕልም ብቻ ነው፤ ርዕይ የሌለው ተግባር ደግሞ ጊዜ ማሳለፊያ ነው፤ ርዕይ ከተግባር ጋር ሲደመር ግን ዓለምን መለወጥ ይቻላል” ይላሉ፤ በትናንትናው ዕለት የተሾሙት ሚኒስትሮችም የሰነቁትን ርዕይ ከመደመር ስትራቴጂ ጋር አስተሳሰረው ለመፈጸም ሌት ተቀን በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ይጠበቃል፡፡
የመደመር አመራሮች የዚህን ትልቅ ሀገር ግንባታ ርዕይ ወደ ተግባር በመቀየር የሕዝብን የዕለት ተዕለት ሕይወት የመለወጥ ታሪካዊ አደራ አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) እንዳሉት÷ ሹመት የምቾት ሳይሆን የከባድ ፈተና እና የሥራ ድካም መሆኑን በመገንዘብ፣ አዲሶቹ ተሿሚዎች ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ ኃላፊነቶችን በሙያዊ ብቃት፣ በቅንነት እና በጥበብ እንዲፈጽሙ ይጠበቃል።
የመጀመሪያውና ዋነኛው ተግባራቸው፥ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም እና የዜጎችን ክብር ማረጋገጥ ሲሆን፣ የሥራዎቻቻው ማዕከልም፥ ማገልገልን እንደ ትልቅ ጸጋ የሚያይ መሆን አለበት። ሁለተኛው አደራ፤ ከሌብነትና ከብልሹ አሠራር የጸዳ ተቋም መገንባት ይጠበቅባቸዋል።
ይህም የሀገርንና የሕዝብን ሃብት ከዝርፊያ የመጠበቅና የተጠያቂነት አሠራርን የመገንባት ግዴታን ያካትታል። ከዚህ በተጨማሪ ከፋፋይ የፖለቲካ ትርክቶችን በማስወገድ የመላውን ሕዝብ የጋራ አብሮነት ማጠናከርና ለሀገር ግንባታ ዋነኛ መሠረት የሆነውን አስተማማኝ ሰላም በየአካባቢያቸው በተግባር ለማጽናት ሕዝብን ማስተባበር ይጠበቅባቸዋል።
የኢኮኖሚ ዕድገትን ማፋጠንና የየኢኮኖሚ ዘርፉ ያሉ ስትራቴጂካዊ ሜጋ ፕሮጀክቶችንና የሕዝብን ሕይወት ቀያሪ የልማት ሥራዎችን ሕዝብ በሚጠብቀው ደረጃ በፈጠራ፣ በፍጥነት እና በጥራት ውጤታማ ማድረግ ሌላው ሊተኮርበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የጂኦፖለቲካ ለውጥ በሚታይበት በዚህ ወቅት የሀገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መሠረት መጣል ከአዲሱ ካቢኔ፤ በአጠቃላይም ከመደመር መንግሥት የሚጠበቁ አበይት ተግባራት ናቸው።
የመንግሥት ምሥረታን እና የአዲሱን ካቢኔ ሹመት አስመልክቶ እስካሁን በተለያዩ የመገናኛ አግባቦች በኩል በሕዝብ እየቀረቡ ያሉ አስተያየቶችና የመልካም ምኞት መግለጫዎች የሚያመላክቱት÷ ሕዝቡ አዲስ በተመሠረተው የመደመር መንግሥት ላይ ከፍተኛ ተስፋና ጠንካራ እምነት እንዳለው ነው።
ብዙዎች አስተያየት ሰጪዎች አዲሱ ሀገራዊ ኃላፊነት፣ አዲስ ትጋትና የላቀ ውጤት ይዞ እንደሚመጣ በማመን ለአዲሱ የመደመር መንግሥት አመራሮች ስኬታማ የሥራ ዘመን ተመኝተዋል።
የትልቅ ሕዝብ እና የትልቅ ሀገርን ታላቅ ርዕይ ለመፈጸም ታሪካዊ ዕድል ያገኙት አመራሮች የሕዝብን አደራና የመንግሥትን ኃላፊነት በቅንነትና በአገልጋይነት መንፈስ እንደሚወጡት እምነታቸው ሙሉ እንደሆነም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደሚሉት÷ የትልቅ ሀገርንና የትልቅ ሕዝብን ታላቅ ርዕይ ለመፈጸም የተዘጋጀ አመራር ሥልጣኑን እንደ ጊዜያዊ አደራ እንጂ እንደ ቋሚ ንብረቱ አይቆጥርም፤ መቁጠርም የለበትም። የአገልጋይነት ሥነ-ምግባር የተላበሰ መሪ ኮፍያው በማንኛውም ሰዓት ሊወልቅ እንደሚችል ተረድቶ፣ የሕዝብን አደራ በታማኝነት፣ በፍትሐዊነት፣ በቅንነትና በውጤት በመምራት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የከፍታ ማማ ለማሻገር የበኩሉን ዐሻራ እንደሚያኖር ይጠበቃል።
በአሰፋ አሕመድ
Exit mobile version