አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሙስና ሀገርን ወደ ኋላ የሚጎትት፣ የታላቅነት ጉዞ እንቅፋት ነው፡፡ የሀገርን ሀብት በማባከን ማህበረሰቡ የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝም ያደርጋል፡፡
የመደመር መንግሥት እነዚህን ብልሹ አሰራሮች ለመከላከልና እምነት ያላቸው ተቋማትን ለመገንባት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የተቋማትን አሰራር በዲጂታል መልክ በማዘመን የሌብነት ተጋላጭነትን ለመቀነስ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
እንዲሁም የተለያዩ ምርመራዎችን በማካሄድ በወንጀል ተሳትፈው የተገኙ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በ2018 ዓ.ም በተደረገው ምርመራም ከ1 ሺህ 600 በላይ የሙስና መዝገቦች ተመርምረዋል፤ እንዲሁም ከ300 በላይ መዝገቦች ተከፍተው ከ400 በላይ ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
በትናንትናው ዕለት በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛ የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለቦታው ይመጥናሉ ያሏቸውን የመደመር መንግሥት ካቢኔ አባላትን አቅርበዋል። ምክር ቤቱም ሹመቱን መርምሮ አጽድቋል።
የሚኒስትሮች ሹመት ብቃትን መሠረት ያደረገ እና አካታችነትን ያረጋገጠ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን በተሻለ ሁኔታ ወደ ፊት የሚወስዳትና ከግቧ የሚያደርሳት ነው፡፡
ሹመቱ ሀገር በኃላፊነት የሚሰጣቸው ሰዎች ምን ያህል ከሙስና የፀዱ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አካባቢያቸው ላይ የሚፈጸሙ የሙስና ተግባራትንና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል ያላቸው ዝግጁነት ተጠንቶና ተፈትኖ የተደረገ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ሁሉም ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች ላለፉት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ ሚስጥራዊ ክትትል ሲደረግባቸው ቆይቷል፡፡
በተጨማሪም በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ያላቸውን እንቅስቃሴ፣ ከልጆቻቸው፣ የትዳር አጋሮቻቸው፣ ከሚያገኟው ሀብታሞች ጋር በሙሉ ምስጢራዊ ክትትል ሲደረግ ቆይቷል፤ በሙስና ተጠርጣሪነት ያላቸው ሚኒስትሮች ወደ ካቢኔ አባልነት ፈፅሞ አልተካተቱም ብለዋል፡፡
በትናንትናው ዕለት ሹመት የተሰጣቸውና ሀገር ለማስተዳደር ኃላፊነት የተጣለባቸው ሁሉ ስልጣናቸውን በአግባቡ ህዝብን ለማገልገል የሚጠቀሙ ከመሆናቸው ባሻገር ለትውልዱ አርዓያ መሆን እንደሚገባቸው ይታመናል፡፡
በመሆኑም ይህ ውሳኔ መንግሥት የሀገርን አደራ የሚወጡ፣ ሸክሟን ተሸክመው ሊያቀሉላት የተዘጋጁ ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ በመንግሥትና በዜጎች መካከል መተማመንን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ካቢኔዎችን በመሾም ለኢትዮጵያ ይበል የሚያሰኝ ስራን መስራቱን ያሳያል፡፡
በቤተልሔም ግርማ

