አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራቸው ነገሮች አንዱ የሆነው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂክ እቅድን መሠረት አድርጎ አገልግሎት የሚሰጠው የመሶብ አንድ ማዕከል ይጠቀሳል፡፡
ዜጎች አገልግሎቶችን ማግኘት ሲፈልጉ በርካታ ቦታዎች መድረስና ውጣውረዶችን ማለፍ ይገባቸው ነበር፤ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ አካትቶ በመያዝ ይህን የሚያስቀር ሥርዓት የዘረጋ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ለነዋሪዎች የሚያስፈልጓቸውን አገልግሎቶች ለማግኘት የሚሄዱበት መንገድ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን የሚያባክን ነበር፡፡
ዛሬ ላይ መሶብ እንደስሙ ብዛት ያላቸው አገልግሎቶችን አቀናጅቶ በመያዝ ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ መስኮት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እንዲያገኙ ያስቻለ ነው፡፡
የእነዚህ አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ላይ መገኘት ዜጎችን እንግልት ሲዳርግ፣ ኢኮኖሚያቸውን ሲያዳክም የቆየውን ዘመናዊነት የጎደለውን አሰራር የቀረፈ ነው፡፡
በተጨማሪም የተቋማትን ቢሮክራሲ የበዛበት ሂደትና ለሙስና ተጋላጭነትን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ውጤትን አምጥቷል፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል በተቋማት መካከል በቅንጅት የመስራትና ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር አስችሏል፡፡
ዜጎች ስለሚያገኟቸው አገልግሎቶች በቂና ግልፅ መረጃን ያገኛሉ፣ ይህም በተቋማት ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ ያግዛቸዋል፡፡
መነሻው ላይ ከነበረው አዳዲስ መልኮችን ጨምሮ በተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎትና በሞባይል ስልኮች አማካኝነት ለዜጎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)የኢኮኖሚ ወሳኝ መሠረተ ልማት የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፤ የዜጎችን ጊዜ ይቆጥባል፣ የሙስና ቀዳዳዎችን ይደፍናል እንዲሁም በመንግሥት በኩል የተቋማትን ታማኝነትና ጥንካሬ ያጎለብታል ማለታቸው ይታወሳል።
በመሆኑም ይህ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግሥት ለሚያሳካው የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ እንዲሁም ተቋማትን የማዘመንና ዲጂታል አሰራሮችን የመከተል ሂደት ዜጎችን ከእንግልት እየታደገና ሀገርን በዘመናዊነት ጎዳና እያራመደ ይገኛል፡፡
#የመደመር_መንግሥት
በቤተልሔም ግርማ

