አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ የማዕድን ሃብቷን በአግባቡ መጠቀም እንድትችል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በመደመር እሳቤ የማዕድን ሀብትን በማልማት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያስመዘግብ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
የማዕድን ዘርፉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው አምስት ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ለግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለኮንስትራክሽንና ለሌሎች ዘርፎች ግብዓት የሚሆኑ እምቅ የማዕድን ሀብቶች ባለቤት ናት፡፡
መንግሥት ያለውን ሀብት የመለየትና ከሀገራዊ ፖሊሲ ጋር የማስማማት ስራ በመስራቱ በዘርፉ ያለው ኢንቨስትመንት ከመቼውም ጊዜ በላይ አድጓል፡፡
በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ወደ ስራ የገባው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ አጋርነት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው ብሔራዊ
የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ የመደመር መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት የሚያሳይ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፋብሪካው በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማንጠር አቅም ያለው መሆኑን ተቅሰው፤ ይህ የማጣሪያ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት ለመጨመር፣ የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ ለማጠናከር እና ሀገራችንን በውድ ማዕድናት ማጣሪያ ረገድ ቀጣናዊ ማዕከል ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ይህ ውጥን፤ ሀብቶቻችንን ከኢንዱስትሪ አቅም ጋር በማስተሳሰር ወጭ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ የሰለጠነ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የጌጣጌጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ፣ እንዲሁም ይበልጥ ግልጽ እና ተወዳዳሪ የሆነ የወርቅ እሴት ሰንሰለት ለመገንባት የመደመር መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት።
ከማዕድን ማውጣት እስከ ኢንዱስትሪ ሽግግር ድረስ በሀገራችን ውስጥ የላቀ እሴት እየፈጠርን እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል፡፤
በዘርፉ የተከናወነው ስር ነቀል የእይታ ለውጥ በዋናነት ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ አሳድጓል፡፡
የመደመር መንግሥት በዘርፉ ያደረገው የእይታ ለውጥ ከገቢ ምንጭነት ባለፈ ለፋብሪካዎችና ግንባታዎች የሚፈለጉ ማዕድናትን በሀገር ውስጥ አምርቶ መጠቀም አስችሏል፡፡
ይህም ሀገሪቱ የነበረባትን የውጭ ጥገኝነት በመቀነስ ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተ ሲሆን፤ የማዕድን ምርትን በሀገር ውስጥ በስፋት መጠቀም ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ ነው፡፡
የማዕድን ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቅድሚያ የሚሰጠው አምራች ዘርፍ ሲሆን፤ ይህ ተነሳሽነት የሀገሪቱን ሀብቶች ከሀገር ውስጥ ማቀነባበሪያ፣ ከኢንዱስትሪ አቅም እና ዘላቂ እሴት ፈጠራ ጋር ለማስተሳሰር የመደመር መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

