አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 ()ኤፍ ኤም ሲ) የዛሬን ስኬት ወደ ዘላቂ ብሔራዊ ብቃት እየቀየርን የጋራ ሀገር ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ከገባነው ቃል በላይ በመፈጸም ያስመዘገብነውን ስኬት መነሻ በማድረግ፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ከበፊቱ የላቀ ዉጤት ለማምጣት የ5 ዓመት እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ አዘጋጅተን የላቀ ለዉጥ ለማምጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የሥራችን ስኬት የሚመዘነው በተሠሩ ሥራዎች ብዛት ብቻ አይደለም ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ዋናው መመዘኛ የሕዝባችንን የኑሮ ጫና ምን ያህል እያቀለልን ነዉ፣ አገልግሎቶችን ምን ያህል አሻሽለናል፣ ለወደፊትስ የሚቀጥል ምን ዓይነት ተቋማዊ አቅም ገንብተናል የሚለው ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት እንደ መሆናችን የተቋማትን፣ የሀብቶችንና የእውቀትን አቅም በማቀናጀት፣ የዛሬን ውጤት ወደ ነገ አቅም፣ የዛሬን ስኬት ወደ ዘላቂ ብሔራዊ ብቃት እየቀየርን የጋራ ሀገር ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን ብለዋል።
አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ከተሞች ምሳሌ፣ ከዓለም ከተሞች ጋር ተወዳዳሪና ለሕዝቧ የተሻለ ኑሮ የምታረጋግጥ ከተማ መሆን እንዳለባት ገልጸዋል፡፡
ይህንንም የምናረጋግጠው በተቀናጀ አመራር፣ በጠንካራ ተቋማትና በሰዉ ተኮር አፈጻጸም ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የዛሬ ሥራችን የነገ አቅማችን ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች የዛሬ ውጤታችን የነገ የኢትዮዽያ ሥልጣኔ መሠረት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

