አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሕዝቡ የተገቡ ቃሎች በተግባር እንዲተረጎሙ የታቀዱ ተግባራት በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የአፈጻጸምና የክትትል ሥርዓት ይጠናከራል አሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)።
የክልሉ መንግሥት መስተዳድር ምክር ቤት በ34ኛ መደበኛ ስብሰባው የቀጣይ 100 ቀናት ዕቅድ በጥልቀት እየገመገመ ይገኛል።
ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በመድረኩ እንዳሳሰቡት፤ አመራሩ የተሰጠውን የሕዝብ አደራ በቁርጠኝነት መወጣትና የሕዝቡን ተስፋ ወደ ተጨባጭ ውጤት መቀየር አለበት።
አመራሩ ሕዝቡን በማዳመጥ የሚነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ የሚፈታ ሥርዓት መገንባት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ የከተሞችን ትራንስፎርሜሽን ማፋጠንና የፕሮጀክት አፈጻጸምን ማሻሻል እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለሕዝቡ የተገቡ ቃሎች በተግባር እንዲተረጎሙ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የሥራ አፈጻጸምና የክትትል ሥርዓት እንደሚጠናከርም አስገንዝበዋል።
ግብርናን በማዘመን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የሥራ ዕድልን ማስፋትና የወጪ ንግድ ምርትን ማሳደግ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የገቢ አማራጮችን በማስፋት፣ የመንግሥት ሀብትን በተሻለ ሁኔታ በማሰባሰብና የግሉ ዘርፍ በኢንቨስትመንት እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የክልሉን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳደግ የሥራ አቅጣጫዎቹ አካል መሆናቸውን አመልክተዋል።
የትምህርት ጥራትን በማሻሻል በእውቀትና በክህሎት የተገነባ ዜጋ ማፍራት የትኩረት ማዕከል መሆን እንዳለበት ተጠቁሟል።
የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን ማጠናከር፣ የመንግሥት ተቋማትን አቅም መገንባትና ለሕዝቡ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ማሻሻል ከተቀመጡት የሥራ አቅጣጫዎች መካከል ናቸው።
የቱሪዝም ዘርፍን ማሳደግ፣ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣ የጋራ ትርክትን መገንባትና የተለያዩ ባህሎችንና እሴቶችን በመጠበቅ የሕዝቡን አንድነትና አብሮነት ማጠናከር የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸው ተመላክቷል።
በመለሰ ታደለ

