አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ይህ ጊዜ የኢትዮጵያ የመነሳት ዘመን ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ አጋርነት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ ጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት፣ በቡና ምርት እና በሌሎችም በከበሩ ማዕድናት የበለጸገች ሀገር ብትሆንም ሃብቶቿን በጥሬ በመላኴ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ በ8 ዶላር የሚሸጠው ቡና ሌሎች ሀገራት ጋር ሲደርስ ከ 30 እስከ 50 ዶላር ያወጣል ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ጥሬ ምርት ልካ የበሰለ ከመቀበል ለመላቀቅ እና የውጭ ምንዛሬ እድገቷን ለማፋጠን እየሰራች ነው ብለዋል፡፡
በማዳበሪያ ፋብሪካ የጀመርነውን ስራ በወርቅ ማጣሪያ ደግመነዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)በሌሎችም ዘርፎች እንዲህ አይነት ስራዎችን በመስራት ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 5 እና 10 ዓመታት ጥሬ ልኮ የበሰለ መቀበልን ታቆማለች ብለዋል፡፡
የተከፈተው የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ ከአፍሪካ እንደኛ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች ሀገራትም ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ የሚችሉ የወርቅ ምርቶች እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡
በ51 ከመቶ ሼር እና በ49 ከመቶ አጋር ተቋም የተከፈተው የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ በዓመት 80 ቢሊየን ዶላር ኤክስፖርት ማድረግ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
ይህ ጊዜ የኢትዮጵያ ትንሳኤ፣ የኢትዮጵያ መነሳት ዘመን በመሆኑ የምንሰራችው ስራዎች ካለምንም ጥርጥር የምናስበውን የብልጽግና ጉዞ፣ የምናስባትን ኢትዮጵያ፣ ሰልጥና የአፍሪካ አርዓያ ሆና የማየት መሻታችንን ለማሳካት የሚያስችል የሚያኮራ ስራ ነው ብለዋል፡፡
በእመቤት ሲሳይ

