አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማጠናከር በቁርጠኝነት ይሰራል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
በኦሮሚያ ክልል በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የእውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመርሐ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ትምህርት የወደፊት ዕድልን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባትና በሁሉም መስክ ቀዳሚ ሆኖ ለመቀጠል ወሳኝ መሣሪያ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት ዓመታት ለትምህርት ዘርፍ በተሰጠው ትኩረትና በተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡
በራሱ የሚተማመንና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት ጥራት ያለው፣ ተደራሽና ፍትሐዊ የትምህርት ሥርዓት እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በትምህርትና ቴክኖሎጂ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ፈጣሪ ትውልድ ለመፍጠር የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማጠናከር እንዲሁም የመምህራንን አቅም ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
ተሸላሚ ተማሪዎች ያመጡት ውጤት የሕዝብ መሆኑን በመገንዘብ በቀጣይ የሚጠብቃቸውን ኃላፊነት በሚገባ እንዲወጡ ማሳሰባቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

