አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዚህች ታላቅ ሀገርና ታላቅ ሕዝብ እንዲሁም ትልቅ ርዕይ ላለው መንግሥት የሚመጥን የፖሊስ ኃይል ለመገንባት የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው አሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል።
ልዩ ኦፕሬሽን ስልጠና የወሰዱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት በአፋር ክልል አዳይቱ ልዩ የኦፕሬሽን ስልጠና ማዕከል ተመርቀዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ እንዳሉት÷ ለዚህች ታላቅ ሀገርና ታላቅ ሕዝብ እንዲሁም ትልቅ ርዕይ ላለው መንግሥት የሚመጥን የፖሊስ ኃይል ለመገንባት የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው።
በዚህም የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት ለማወክ የሚንቀሳቀሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ላይ የሚሰጠውን ፖሊሳዊ ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚችያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከለውጥ ወዲህ የሀገሪቱን ፖሊስ ለማዘመን እየሠራ ከሚገኛቸው ሥራዎች አንዱና ዋናው የኦፕሬሽን አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የተለያዩ የስፔሻላይዜሽን ስልጠናዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም መናገራቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።
የዛሬ ተመራቂዎችም በአስቸጋሪ የአየር ፀባይ እና የመሬት አቀማመጥ የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ፖሊሳዊ ግዳጅ ለመወጣት የሚያስችል በተግባር የተደገፈ ስልጠና ውስጥ ያለፉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

