Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል ልማት ለቀጣናዊ ትስስር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል ልማት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ከማፋጠን ባለፈ ለቀጣናዊ ትስስርና ትብብር ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው።

የኢትዮጵያ የውሃ፣ ፀሐይ፣ ነፋስና ጂኦተርማል ብዝኅ የኃይል ፀጋዎች ልማት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን ማጎልበት የሚቻልበትን ምኅዳር እየፈጠረ ይገኛል፡፡

የታዳሽ ኃይል ልማት እመርታዊ ጉዞ የኤሌክትሪክ ማመንጨትን ከልማት፣ ከኢኮኖሚ ዕድገት እና ከቀጣናዊ ትስስር ጋር እያሰናሰለ የሚገኝ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ግብ አካል ነው።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ምርትን እያሳደገ የሚገኘው ታዳሽ ኃይል ልማት ÷ለጎረቤት ሀገራት የኃይል አቅርቦትን ከማረጋገጥ ባለፈ የኢኮኖሚ ትስስርን፣ የጋራ ተጠቃሚነትንና የቀጣናውን ትብብር ለማጠናከር አዳዲስ ዕድሎችን እየፈጠረ ነው።

ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገትና የኢንዱስትሪ ሽግግር እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልጽግና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሪነት የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚያሰፉና የሚያዘምኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነች ትገኛለች።

ይህ ስትራቴጂካዊ ጉዞ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከጨለማ ከማውጣት ባለፈ ሀገሪቱን የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል ለማድረግ ያለመ ታላቅ ብሔራዊ ራዕይ ነው።

የዚህ ግዙፍ የኃይል መሠረተ ልማት ግንባታ ግንባር ቀደም ተምሳሌት የሆነው የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የጽናት፣ የጥበብ፣ የአብሮነትና የመተባበር መገለጫ ነው።

ግድቡ የዓባይን ወንዝ ተፈጥሯዊ ፍሰት ሳይገታና የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ጥቅም ሳይነካ የውሃውን ኃይል ወደ ንጹህ የኤሌክትሪክ ብርሃንነት በመቀየር ረገድ ታሪካዊ ምዕራፍ እየፈጠረ ይገኛል።

ግድቡ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ለከተሞች መስፋፋትና ለገጠር አካባቢዎች የብርሃን ምንጭ በመሆን የኢኮኖሚውን ሞተር በማንቀሳቀስ ላይ ነው።የኢትዮጵያ የኃይል ስትራቴጂ በውሃ ሃይል ወይም በሕዳሴው ግድብ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም።ሀገሪቱ የኃይል ምንጮቿን ከማስፋት ረገድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።

በውሃ ኃይል እንደ ኮይሻ፣ ግልገል ጊቤ እና ሌሎች የወንዝ ተፋሰሶች ላይ የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ሜጋ ዋት ሀይልን ለብሔራዊ ኃይል ቋት እያበረከቱ ናቸው።

ከዚህም በተጓዳኝ፣ ኢትዮጵያ ካላት የተፈጥሮ ጸጋ በመነሳት የንፋስ ኃይል፣ የፀሐይ ብርሃን ኃይል እና የምድር ውስጥ እንፋሎት ልማቶችን በስፋት እያከናወነች ትገኛለች።

እንደ አሸጎዳ እና አዳማ ያሉ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች እንዲሁም የአሉቶ ላንጋኖ የምድር ውስጥ እንፋሎት ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ታዳሽ ኃይል ይበልጥ አስተማማኝ እና ከተፈጥሮ መዛባት የተጠበቀ እያደረጉት ይገኛሉ።

ይህ በሀገር ውስጥ የሚመነጨው ግዙፍ የኃይል አቅም ከኢትዮጵያ ድንበር አልፎ ቀጣናዊ ትስስርን ለመፍጠር ትልቅ መሣሪያ እየሆነ ነው።ኢትዮጵያ “የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ማማ” የመሆን ራዕይዋን ለማሳካት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን በመዘርጋት ላይ ናት፡፡

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ከተለያዩ የሃይል ምንጮች 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መቻሏን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ሽያጭ እያቀረበች ሲሆን÷ ይህም ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ በቀጣናው ሀገራት መካከል ያለውን የትብብር፣ የሰላምና የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ከማጠናከር አንጻር ጉልህ ፋይዳ አለው፡፡

Exit mobile version