አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሠንደቅ ዓላማችን የመደመር ዕሴታችን፣ የአንድነታችንና የኢትዮጵያ ከፍታ ምልክታችን ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፈፉት መልዕክት፤ ዛሬ 19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን አክብረናል ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማ የቀደምት አባቶቻችንን የመሥዋዕትነት ታሪክ የሚያስታውሰን፣ የዛሬ ትጋታችንን የሚያንፀባርቅና የነገውን የብልፅግና ራዕያችንን የሚያመላክት የሀገራችን የከፍታ ዓርማ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት ዋነኛ ትኩረት ኢትዮጵያን በአንድነት፣ በሰላም፣ በልማትና በሁለንተናዊ ብልጽግና ወደ ላቀ ከፍታ ማሸጋገር እንደሆነም አብራርተዋል።
ሠንደቅ ዓላማችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን መገለጫ እንጂ የልዩነታችን ምንጭ መሆን የለበትም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህልና በእምነት የተለያየን ብንሆንም፣ በኢትዮጵያዊነታችንና በጋራ የልማት ራዕያችን አንድ ነን ብለዋል።
የመደመር ዕሳቤም ልዩነቶቻችንን እንደ ሀብት በመቁጠር፣ የጋራ ዕሴቶቻችንን በማጠናከርና በትብብር የሀገራችንን ታላቅነት በተግባር ለማረጋገጥ ያነሳሳናል በማለት ገልጸዋል።

