Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሠንደቅ ዓላማ ቀንን የምናከብረው በምናስመዘግበው ስኬት ጭምር ነው – ወ/ሮ ቡዜና አልከድር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሠንደቅ ዓላማ ቀንን የምናከብረው በሥነ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን በምናስመዘግበው ስኬት ጭምር ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር።
19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን!” በሚል መሪ ቃል በዐድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ ወ/ሮ ቡዜና እንደገለጹት÷ የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ማክበር በዓሉን በሥነ ሥርዓት ከማክበር ባለፈ ለሀገር በምንወስደው ቁርጠኝነት፣ በምንፈጽመው ተግባርና በምናስመዘግበው ውጤት የሚገለጽ ነው።
በዓሉ የጋራ እሴቶቻችንን፣ የመተሳሰብ መንፈሳችንንና የሀገራዊ መግባባትን አስፈላጊነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ብሔራዊ መግባባት የጋራ እድገትና ብልጽግና መሠረት በመሆኑ፣ የከተማዋን እድገትና የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሁሉም በትጋትና በትብብር በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
ለሀገር ሰላምና ደኅንነት፣ ለሕዝብ ጥበቃና ለሉዓላዊነት መጠበቅ መስዋዕትነት የከፈሉና አሁንም በትጋት እያገለገሉ ያሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን፣ የጸጥታ አካላትንና ሌሎች የሀገር አገልጋዮችን ማመስገናቸውን የከተማዋ ከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያሳያል።
በበዓሉ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ቡዜና አልከድርን ጨምሮ፣ የምክር ቤቱ አባላት፣ የከተማዋ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ ጀግኖች አርበኞች፣ የጸጥታ መዋቅር አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጥበብ ባለሙያዎችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎችም ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ፣ የሕዝቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ኢትዮጵያን በልማትና በዴሞክራሲ ጎዳና እንድትራመድና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከበለጸጉ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ እና የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ግቦችን ለማሳካት በአንድነትና በትብብር ለመሥራት በሠንደቅ ዓላማቸው ፊት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።
Exit mobile version