አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አስተማማኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር ምህዳር መገንባት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
“ንቁ ዜጋ ደህንነቱ ለተጠበቀ ሀገር!” በሚል መሪ ሃሳብ 7ኛው የሳይበር ደህንነት ወር የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ አሁን ባለው የቴክኖሎጂ ውድድር ወደ ኋላ እንዳትቀር ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች እንደምትገኝ አንስተዋል፡፡
የዲጂታል ምህዳሩ የሀገራት የኢኮኖሚ ጥንካሬና የምርታማነት ዋና ምንጭ፤ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ህይወት ማቃለያና የአገልግሎት ቅልጥፍና ማረጋገጫ እንዲሁም የሀገራዊ ሉዓላዊነትና የብሔራዊ ደህንነት መጠበቂያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንደ ሀገር የተቀረጸው “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ ሀገራችንን ወደ ዘመናዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሸጋገር እንደ ጠንካራ ድልድይ ሆኖ አልፏል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የሳይበር ምህዳሩ ከመሬት፣ ከባህር፣ ከአየር እና ከህዋ ቀጥሎ አምስተኛው የዓለም አቀፍ ጦርነትና የኃይል ሚዛን መፈተሻ አውድ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምትገኝበት የቀጣናው ነባራዊ ሁኔታ እና የጂኦ ፖሊቲካል ተፎካካሪነት ለሳይበር ጥቃት ያለንን ተጋላጭነት ከፍ ያደርገዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሳይበር ወንጀለኞች እና የኢትዮጵያ ጠላቶች የጥቃት ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
የኃይል ማመንጫዎች፣ የቴሌኮም ማዕከላቶች፣ የትራንስፖርትና የአቪዬሽን ሥርዓቶች እንዲሁም የፋይናንስ ተቋሞች የሳይበር ጥቃት ሙከራ ሊደረግባቸው እንደሚችልም አንስተዋል።
በመሆኑም የሳይበር ደህንነት የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን በመረዳት ሁሉም ለሳይበር ደህንነት መረጋገጥ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በለይኩን ዓለም

