Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተዘጉ አገልግሎቶች መመለሳቸው እና እንቅስቃሴ መጀመሩ ተስፋ ሰጥቶናል – የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የተዘጉ አገልግሎቶች መመለሳቸው እና እንቅስቃሴ መጀመሩ ተስፋ ሰጥቶናል አሉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች።

በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የተለያዩ የአገልግሎት ተቋማት እንደገና መከፈታቸውና የንግድ እንቅስቃሴው መሻሻሉ ለትግራይ ሕዝብ የተስፋ ብርሃን እየፈነጠቀ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ አቶ እዮብ አብርሀ÷ ከዚህ ቀደም እንቅስቃሴዎች ተገትተው እንደ ነበር አንስተው አሁን አየር መንገድ ፣ባንኮች እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጭ ተቋት ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በህዝቡ ውስጥ የነበረው ፍርሃት እየረገበ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ካህሳይ ተካ ናቸው፡፡

ሼህ ኦላ መለስ በበኩላቸው÷ ከዚህ ቀደም ሱቆች ዝግ በመሆናቸው መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ ሱቆች ወደ ሥራ እየተመለሱ ነው ሲሉ አንስተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አፈሳ ምክንያት ለማንፈልገው ጦርነት እንገደድ ስለነበር በእርሱ ምክንያት ከቤቱ የሚወጣ ወጣት አልነበረም ያሉት አቶ ዳንኤል መለስ አሁን ላይ ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰች መሆንዋን አብራርተዋል፡፡

የከተማዋ ሰላም ለሕዝቡ ዕለታዊ ኑሮ፣ ለንግድ እንቅስቃሴውና ለአጠቃላይ ልማት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ነዋሪዎቹ የተገኘውን ሰላም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በትብብር አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በእመቤት ሲሳይ

Exit mobile version