Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ተመልከት ሠንደቅህን፣ ተከተል አለቃህን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ይህች ሰንደቅ ከጨርቅ በላይ ናት። ዓድዋ ላይ በደም የተነከረች፣ በወረራ ጨለማ ያልጠፋች፣ ከጋና እስከ ሴኔጋል በርካታ አፍሪካውያን የነጻነታቸውን ሠንደቅ ሲሰፉ ቀለሟን የቀዱላት ናት።

ይቺን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ጠላት ደጋግሞ ሊጥላት ሞከረ፤ ነገር ግን በአይበገሬ ጥቁር አናብስት ልጆቿ ጽናት ዛሬም ከፍ ብላ ከመውለብለብ አላስቀራትም።

ዛሬም ሊጥሏት የሚሞክሩ አሉ። አይችሏትም። የልጆቿ ክንድ እሳት ነው፤ ቋያ ነው! ሊጥሏት የሚሞክሩ ቀድመው ይወድቃሉ። እየወደቁ ነው!

ሠንደቅ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ሠንደቅ! አይነጣጠሉም። አይተጓጎሉም። የኢትዮጵያውያን ብሒላቸውም «ተመልከት ሠንደቅህን፣ ተከተል አለቃህን» ነው።

ጥልቅ መልዕክት፣ ሁለት ትእዛዝ፣ ሁለት ድርሻ የያዘ ብሒል!

“ተመልከት” የሕዝብ ነው፤ ዓይንህን ከሚከፋፍል ጊዜያዊ ሁከት አንሥተህ ወደ ሁላችን ምልክት አቅና፣ ሀገርህን እያት የሚል ነው ቁልፍ መልዕክቱ።

“ተከተል” የመንግሥት አደራ ነው፤ ሠንደቁ ይቀድማል፣ አለቃ ይከተላል። መሪ ሠንደቅን በከፍታው ላይ የሚያፀና መንገድን ይጠቁማል፣ ህዝብ ለሠንደቁ ክብር አባሪ ተባባሪ ይሆናል።

መሪና ተመሪ ሲያብር ሲተባበር ጠላት ይተናል፤ ምቀኛ ይበናል። ሠንደቅ ትከብራለች። ግን ማስጠንቀቂያም አለው። መሪ ለሠንደቁ ካልሰራ ሠራዊት የለውም።

ሠንደቅን ተመልከቱ። ጨርቅ ያለ ምሰሶ መሬት ላይ ይወድቃል፤ ምሰሶ ያለ ጨርቅ ባዶ ዱላ ነው። ሕዝብ ጨርቁ ነው፣ መንግሥት ምሰሶው፤ ሁለቱን የሚያስተሳስረው ቋጠሮ እምነት ነው።

መናበብ ማለት እንደ ክራርና መሰንቆ በአንድ ዜማ መገናኘት ነው። ዓድዋም የሕዳሴ ግድብም ይህን መናበብ መስክረዋል።

መናበብ ማጨብጨብ ብቻ አይደለም። ሕዝብ ሲጠይቅና ሲተች፣ መንግሥት ሲያዳምጥ ቋጠሮው ይጠብቃል።

ሕዝብ ሆይ፣ ሠንደቅህን ተመልከት። መንግሥት ሆይ፣ ሠንደቁን የሚያይ አለቃ ሁን። ያን ጊዜ ሠንደቋ አትወድቅም። በጠላቶች መውደቅ ላይ ከፍ ብላ ትውለበለባለች!

ስለዚህ “ተመልከት ሠንደቅህን፣ ተከተል አለቃህን!”

በአፈወርቅ እያዩ

Exit mobile version