አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ከምሰሶው በብዙ ርቀት ከፍ ብሎ የሚታይ የኩራታችን ምንጭ፤ የኢትዮጵያውያን ህያው መታያ ቀለማችን ነው፡፡
የታላቅነታችን ምልክት የሆኑትን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት የምናውቃቸው ገና በልጅነት በተኮላተፈ አንደበት ብሔራዊ መዝሙራችንን ስንዘምር ነው፡፡
ያኔ ሽቅብ አንጋጥጠን እያየን ከምሰሶው ጫፍ እስኪወጣ በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው ሰንደቃችን፤ ከምሰሶው ባሻገር አድማሳትን ሰንጥቆ ዓለማትን የሚያካልል ህያው መታያችን ነው፡፡
ይህች ሠንደቅ ዓላማ ስናያት የምንሳሳው፤ የሀገር አለኝታና ጠንካራ ዘብ የሆኑት የኢትዮጵያ ወታደሮች ስለሕዝባቸው ነጻነትና ስለሀገራቸው ሉዓላዊነት ነፍሳቸውን ሳይሰስቱ የሞቱላት በመሆኗ ነው፡፡
ሠንደቅ ዓላማችን ክብራችንና ኩራታችን ነው ስንል፤ በዓለም አደባባይ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማትን በከፍታ የሚያውለበልበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቶውንም ሊዘነጋ አይችልም፡፡
ከስምንት አስርት ዓመታት በላይ ሰማዩን እየቀዘፈ፤ የኢትዮጵያ ኩራትም ራትም ሆኖ ፈተናዎችን በድል እየተሻገረ፤ ሳይዋዥቅ የዘለቀው ይህ የሀገር ሀብት ከሰንደቋ ተለይቶ አይታይም፡፡
የአፍሪካውያን ጭምር የኩራት ምንጭ የሆነው አየር መንገዱ ታህሳስ 1 ቀን 1938 ዓ.ም እንደተመሰረተና በዚያው ዓመት መጋቢት 30 የመጀመሪያ በረራውን ከአዲስ አበባ ወደ ካይሮ ማድረጉን ታሪክ መዝግቦታል፡፡
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን፣ ሕዝቧንና ሠንደቋን ከፍ አድርጎ፤ በዓለም አደባባይ መታያዋ ሆኖ ዘልቋል፡፡
አየር መንገዱ ዛሬም ከአፍሪካ ቀዳሚው ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፤ 25 የሀገር ውስጥ እንዲሁም በአራት አህጉራት በ126 መዳረሻዎች በረራዎችን እያደረገ ይገኛል።
የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት፤ የፓን አፍሪካኒዝም ምልክት የሆነችው ኢትዮጵያ፤ የከፍታ ጉዞዋን ላታቋርጥ ጀምራለች፤ ሠንደቋም በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ ይውለበለባል።
80 የከፍታ ዓመታትን ያሳለፈው አየር መንገዳችንም ዘመኑን እየዋጀ በዓለም ፊት መታያችን፤ የሀገራችን ኢኮኖሚ ደጋፊ በመሆን የሀገሩን ሠንደቅ አትሞ ይዘልቃል።
በኃይለማርያም ተገኝ

