አዲስ አበባ፣ ጥቅምት3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ወደ ተሻለ ውጤት ለማሸጋገር፣ በብዝሃ ፖለቲካ ውስጥ ብዝሃ ሃሳቦችን ለማስተናገድ እና በዓለም መድረክ ብሔራዊ ጥቅሟን በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረች ትገኛለች።
የመንግሥት ምሥረታ በራሱ የመጨረሻ ግብ ሳይሆን፤ የተሰጠን የሕዝብ ኃላፊነት ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀየርበት የሥራ መነሻና ኃላፊነት ነው።
በመሆኑም አዲስ የተዋቀረው የመንግሥት አስተዳደር የሕዝቡን የልማት፣ የሰላም፣ የፍትሕና የተሻለ አገልግሎት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም በመሰነቅ ሊሆን ይገባል።
አዲሱ የመደመር መንግሥት በቀጣይ የኢኮኖሚ መረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ማቃለል፣ የዜጎችን የመግዛት አቅም ማሻሻልና የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ማረጋጋት ይጠበቅበታል፡፡
የኢትዮጵያን የባሕር በር እና የወደብ ባለቤትነት ጥያቄ አሁን እየሰራበት ባለው በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መርሕ መምራት ከአዲሱ መንግሥት የሚጠበቅ ትልቅ የቤት ሥራ ነው።
አዲሱ የመደመር መንግሥት ቀጣይ የቤት ስራ የተቋማት ምሥረታ ብቻ ሳይሆን፤ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በውጤታማነት ማስቀጠል ነው።
ባለፉት ዓመታት በግብርና፣ በመስኖ ልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በቱሪዝም፣ በኃይል ልማት እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች የተመዘገቡ እመርታዎችን በላቀ መልኩ ማስቀጠል ይጠበቅበታል።
የመስኖ ስንዴ ምርትን በማስፋፋት፣ የሌማት ትሩፋትን በማጠናከር፣ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ምርትን በማስፋፋት፣ የማዕድን ሀብትን በአግባቡ በማልማት፣ የዲጂታል ሽግግርን በማፋጠን እና የቱሪዝም ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት በመቀየር ለኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት መትጋት አስፈላጊ ነው፡፡
የሀገር ግንባታ ሂደት የአንድ ጊዜ ስራ ብቻ ባለመሆኑ በተደመረ አቅም በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን ማላቅ እና የተቋማት ግንባታን አጠናክሮ መቀጠልንም ይፈልጋል፡፡
ከባለፉት ዓመታት የተገኙ ስኬቶችን በመቀመር፣ የነበሩ ችግሮችን በማረም፣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናቀቅ እና አዳዲስ ዕድሎችን በመፍጠር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ ማድረስ ሲሆን፤ አዲሱ መንግሥት ብዙ ስራዎች ይጠብቁታል፡፡

