አዲስ አበባ፣ ጥቅምት3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አቅሙ የጎለበተ እና ቅድመ መረጃ የሚሰጥ የሜቲዎሮሎጂ ተቋም መገንባቱ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ተቋሙ አሁን ያለውን ቅርጽ ይዞ የተቋቋመው ከ46 ዓመታት በፊት በፈረንጆቹ 1980 ሲሆን፤ ከዚያ በፊት በአቪዬሽን ስር በዲፓርትመንት ደረጃ የቆየበት ጊዜ ሲደመር ከ70 ዓመታት በላይ የአገልግሎት እድሜ እንዳለው ገልጸዋል።
እንደዚህ ያሉ ተቋማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ተቋማዊ አቅማቸው ካልጎለበተ ሊያስከትሉ የሚችሉት ሀገራዊ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን የ1987ቱን ድርቅ እና የዘንድሮውን የኤልኒኖ ክስተት ለአብነት በማንሳት፤ ሁለቱም ክስተቶች በትንበያ ደረጃ የተቀራረበ ጫና እና ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ እንደነበሩ አብራርተዋል።
የተቋሙ አቅም እየተጠናከረ መምጣቱ፤ መረጃ በጊዜ መስጠቱ እና መንግሥት አስቀድሞ እንዲዘጋጅ ማስቻሉ የጉዳቱን መጠን መቀነስ ማስቻሉንና በውጤት ደረጃም የ1987ቱ ድርቅ እና የዘንድሮው ስኬት የማይወዳደሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አስቀድሞ በተገኘው የሜቲዎሮሎጂ መረጃ መሰረት ለመዘጋጀት እድል በመገኘቱ፤ በዘንድሮው የክረምት ወቅት የታቀደው ትንበያ እና የተገኘው የሰብል ምርት ውጤት አበረታች መሆኑን አስገንዝበዋል።
መረጃ ላይ ተንተርሶ ለማቀድ እና ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት እንደ ኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያሉ ተቋማት አስፈላጊነት በእጅጉ የጎላ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመልካም ፈቃዱ

