አዲስ አበባ፣ ጥቅምት3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል የተጀመሩና አዳዲስ የልማት ሥራዎችን ከሕዝባችን ጋር በመቀናጀት አጠናክረን እንቀጥላለን አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር)፡፡
በክልሉ “የመደመር መንግሥት ምስረታና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫ” በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሀዋሳ ከተማ ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የታገዙ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት በቁርጠኝነት ይሰራል፡፡
የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ተግባራት አማካኝነት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በድጋሚ የሕዝብን ቅቡልነት በማግኘት መንግሥት መመስረቱን አስታውሰዋል፡፡
የሲዳማ ሕዝብ ልማትንና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ረገድ የራሱ ጠንካራ ባህላዊ እሴቶች ያለው ትልቅ ህዝብ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፤ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሰላምን ለማጽናት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የክልሉ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በግብዓትነት በመውሰድ የዕቅድ አካል አድርጎ በመውሰድ ይሰራል ነው ያሉት፡፡
በመድረኩ ላይ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ባለሀብቶች እየተሳተፉ እንደሚገኙ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት መረጃ አመልክቷል፡፡

