አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኃይል ዘርፍ ማዘመኛ የሚውል የ145 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት አጽድቋል።
የብድር ስምምነቱ በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል የተደረሰ ሲሆን፤ አዋጅ ቁጥር 1441/2019 ሆኖ በምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ፍቃዱ ተሰማ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ማብራሪያ እንደገለጹት፥ የተገኘው ብድር ለኃይል ሴክተር ሪፎርም ኢንቨስትመንትና ማዘመኛ ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ነው።
የብድሩ ዋና ዓላማ የአዲስ አበባን የኃይል ማስተላለፊያ መረብ ማጠናከር፣ አዳዲስ የኃይል ጣቢያዎችን መገንባት፣ ነባሮቹን ማሻሻል እንዲሁም የመሬት ውስጥ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን መዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ብድሩ ከሀገሪቱ የብድር አሰጣጥና አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣምና ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑንም አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስነስርዓት ላይ የፌዴራል መንግሥትን ዓመታዊ ዕቅድ በማስመልከት ያደረጉትን ንግግር አስመልክቶ የቀረበ የድጋፍ ሞሽን አዳምጧል።
የድጋፍ ሞሽኑም በምክር ቤት አባል ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፣ በቀጣይ ሞሽኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እንደሚጸድቅ አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

