አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት የሃይማኖት ተቋማት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በየደረጃው ለመፍታት ዝግጅ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በ45ኛው የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ራስን የማስተዳደር ማሳያ ናት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እስከ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ድረስ 6 ፓትርያርኮችን መሾሟን ጠቅሰው፤ ቤተክርስቲያኗ ራስን የማስተዳደር ማሳያ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነገር ቤተክርስቲያን መኖሯን በመግለጽ፤ የሀገራችን ነጻነት ሲከበር ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆኗን አመልክተዋል፡፡
በዓድዋ ጦርነት ዋጋ ለመክፈል መሰለፏን በመጥቀስ፤ የቀደመ ክብር እና ትጋትን በማስቀጠል ቤተክርስቲያኗ አሁንም ያላትን ሃብት ለቀጣይ የሃገር ልማት መጠቀም ትችላለች ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ከልማቱ ጎን ለጎን በግጭት ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ወደ ውይይትና ሰላም እንዲመጡ ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የሃይማኖት ተቋማት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በየደረጃው ለመፍታት ዝግጅ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በለይኩን ዓለም

