አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)በዓለም አቀፍ መድረኮች የውሃ እጥረት አለብኝ የሚል ሰፊ የፖለቲካ ትርክት ለመገንባት የምትሞክረው ግብጽ በእውነቱ የውሃ እጥረት አለባት ወይስ የከፋ የውሃ አስተዳደር ችግርና ከፍተኛ የሃብት ብክነት?
ሀገሪቷ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረሙና ኢትዮጵያን ባገለሉ የ1929 እና የ1959 ውሎች መሠረት 55 ነጥብ 5 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የዓባይን ውሃ በብቸኝነት የእኔ ብቻ ነው ስትል ብትሞግትም፤ የተግባር አጠቃቀሟ ግን የቁጠባ ሳይሆን ከፍተኛ የሃብት ብክነት ያለበት እንደሆነ ያስረዳል።
ሀገሪቱ በዓለም ላይ ከፍተኛ የውሃ ፍላጎት ያላቸውን ሰብሎች በማምረት የዓባይ ወንዝ እንዲባክን ታደርጋለች፡፡ ለአብነት ከፍተኛ የውሃ ፍጆታ ያለውን ሩዝ በማምረት በአፍሪካ ከናይጄሪያ በመቀጠል ሁለተኛዋ ናት፡፡
ግብጽ በየዓመቱ በ650 ሺህ ሄክታር መሬት እስከ 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ሩዝ ለማምረት ከ8 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃን ትጠቀማለች፡፡ ይህም ከዓባይ ወንዝ ላይ ካላት ድርሻ ከ16 በመቶ በላይ የምታውለው ለሩዝ ምርት ብቻ ነው፡፡
130 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለምታመርተው የጥጥ ምርት በየዓመቱ እስከ 700 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃን የምታባክን ሲሆን÷ እንደ ሸንኮራ አገዳ፣ ሙዝ፣ በቆሎና ስንዴ ያሉ ሰብሎችንም በበረሃ ላይ ውሃ በሚያባክን የመስኖ ዘዴ ማምረቷ ከፍተኛ ለሆነ የውሃ ብክነት ይዳርጋታል፡፡
ዓባይ ሕልውናዬ ነው ብትልም የዓባይ ወንዝ በየበረሃው እንዲፈስ በመፍቀዷና በሞቃታማ የአየር ንብረት ምክንያት በየዓመቱ ከ10 እስከ 16 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በትነት እንዲባክን ማድረጓ በእርግጥም ፍትሕ ለዓባይ የሚያስብል ነው፡፡
ግብጽ በሰሜንና በምስራቅ ሰፊ የሜዲትራኒያንና የቀይ ባሕር ዳርቻዎች ባለቤት በመሆኗ፤ የባሕር ውሃን በዘመናዊ የውሃ ማጣሪያ ቴክኖሎጂዎች አጥሎ የመጠቀም ሰፊ ተፈጥሯዊ እድል አላት። ከምድር በታች ከ100 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ የሚገመት ግዙፍ የኑቢያን የከርሰ ምድር ውሃ ባለቤት በመሆኗ፤ አስተማማኝና ዘላቂ የውሃ አማራጮች ያሏት ሀገር ነች።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ አብዛኛው ወንዞቿ ድንበር ተሻግረው የሚወጡባት ከመሆኑም በላይ፤ እንደ ግብጽ የባሕር ውሃን የማጣራት መልክዓ-ምድራዊ አማራጭ የሌላት እንዲሁም የከርሰ ምድር ውሃ ክምችቷም ከግብጽ ጋር ሲተያይ በጣም ዝቅተኛ የሆነ ነው፡፡
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ንጹሕ የውሃ ሀብቷን ጥቅም ላይ ማዋል ግዴታዋ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
ለዚህም ነው የዓባይ ወንዝ መነሻና አፍላቂዋ ኢትዮጵያ ከገዛ ሀብቷ እንዳትጠቀም የመከልከል አካሄድ፤ በዓለም አቀፍ ሕግም ሆነ በተፈጥሮ ሕግ ተቀባይነት የሌለው ታሪካዊ ግፍ ነው የምንለው።
በዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሕግ መሠረት ኢትዮጵያ ውሃዋን በፍትሐዊና ምክንያታዊ መንገድ የመጠቀም ተፈጥሯዊ ዓለም አቀፋዊ መብቷ የተጠበቀ ነው።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘበው የሚገባው መሠረታዊ እውነት የውሃ እጥረት አለብኝ የሚለው የግብጽ አቤቱታ የታሪካዊ ብቸኛ የበላይነትን ይዞ ለመቆየት የሚደረግ የፖለቲካ ካርድ እንጂ እውነተኛ የውሃ እጥረት አለመሆኑን ነው።
ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከድህነት ለማውጣት ዓባይን በፍትሐዊና ምክንያታዊ መንገድ የመጠቀም መብቷ በፍጹም ለድርድር የሚቀርብ አይደለም።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በታሪኩ ለገሰ

