አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከመስከረም 15 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ባለ ሁለት እግር ሞተር ብስክሌት ላይ ተጥሎ የነበረው ክልከላ ተነስቷል አለ የከተማዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ።
ሞተር ብስክሌትን በመጠቀም የተሰረቁ እቃዎችን ከቦታ ቦታ የማዘዋወር፣ ተሽከርካሪዎችን በመግጨት ማምለጥ፣ ሄልሜት ሳያደርጉ ማሽከርከር፣ የተፋፋቀና ለእይታ አስቸጋሪ የሆኑ የሠሌዳ ቁጥሮችን መጠቀምን ጨምሮ የደንብ ጥሰቶች መኖራቸውን በመግለፅ እገዳ መጣሉ ይታወሳል።
የሞተር ሳይከል መንቀሳቀሻ ፈቃድ ያላቸውና መንቀሳቀሻ ፈቃድ ያደሱ ሞተር ሳይከል አሽከርካሪዎች ከነገ ጠዋት ጀምሮ የትራንስፖርትና የትራፊክ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የወጡ ህጎችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱን አስታውቋል፡፡
የመንቀሳቀሻ ፈቃድ የሌላቸውና ፈቃድ ሳያድሱ በሚንቀሳቀሱ የሞተር አሽከርካሪዎች ላይ በህግ አግባብ ርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም አሳስቧል፡፡

