አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገርን ደህንነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የአየር ኃይል ዘመናዊነት፣ የሰው ኃይል ብቃትና የሥራ ዝግጁነት ወሳኝ ሚና አላቸው።
የሀገርን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን፣ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች የመጠቀም አቅም፣ የሰው ኃይል ሙያዊ ብቃት፣ የውጊያ ዝግጁነትና በዲሲፒሊን የተመሠረተ የተግባር አፈጻጸምን ይጠይቃል።
በተለይም የአየር ክልልን መቆጣጠር፣ የድንበር ደህንነትን ማስጠበቅና ለማንኛውም የደህንነት ስጋት በወቅቱ ምላሽ መስጠት የሚችል አቅም መገንባት ወሳኝ ነው።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘመናዊ ቴክኖሎጂን፣ ሙያዊ ብቃትንና ተግባራዊ ዝግጁነትን በማቀናጀት የሀገርን ደህንነት በማስጠበቅ የሚኖረው ሚና የጎላ ነው።
የዘመናዊ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የሰው ኃይል ብቃት ውጤታማ የሚሆነው በተገቢው ሥልጠና በተዘጋጀ፣ ሙያዊ ብቃት ባለውና በወታደራዊ ዲሲፒሊን በታነጸ የሰው ኃይል ሲመራ ነው። ይህም የቴክኖሎጂ አቅምን ወደ ተጨባጭ የሥራ ውጤት ለመቀየር መሠረት ይሆናል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘመናዊነት ከሚገለጽባቸው አቅጣጫዎች አንዱ ከባህላዊ የአየር ውጊያ መሣሪያዎች በተጨማሪ ድሮኖችንና ሌሎች የዘመኑን ቴክኖሎጂዎች የመጠቀም አቅም ነው።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የአየር ክልልን በመቆጣጠር፣ የመረጃ አቅምን በማጠናከርና የሥራ ቅልጥፍናን በማሳደግ ረገድ አስፈላጊ ድርሻ አላቸው፡፡
በኢትዮጵያ ከዓመት በፊት ለሲቪልና ወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን የሚያመርት ስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ መመረቁ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ዘርፈ ብዙ ችሎታ ያላቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በራስ አቅም በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ዲዛይን አድርጎ የማምረት አቅም መፍጠር ለኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነው፡፡
ቴክኖሎጂው የጠላት እንቅስቃሴዎችን በቅጽበት ለመከታተል፣ ጥናት ለማድረግ እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
መሰል አቅምን ይበልጥ ማጠናከርም አየር ሃይል ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን ለመታጠቅ የጀመረውን ጥረት ይበልጥ ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከሥልጠና፣ ከጥገና፣ ከተቀናጀ የመረጃ ሥርዓትና ከተገቢ የውሳኔ አሰጣጥ ጋር ሲጣመር የአየር ኃይሉን ተልዕኮ በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት ያግዛል።
ስለሆነም የአየር ኃይሉ ዘመናዊነት በመሣሪያ ግዥ ብቻ ሳይገደብ፣ የሙያ ክህሎትን በማሳደግ፣ የጥገናና የድጋፍ ሥርዓቶችን በማጠናከርና የተልዕኮ ዝግጁነትን በቀጣይነት በመፈተሽ መደገፍ ይጠይቃል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይ ዋና አዛዥ የሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንደሚሉት÷ የተቋሙ ተግባራዊ ዝግጁነት ማለት በማንኛውም ጊዜ የሚሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም የሚያስፈልጉ ሰው ኃይል፣ ቴክኖሎጂ፣ ሥልጠናና የድጋፍ ሥርዓቶችን በተቀናጀ ሁኔታ ማዘጋጀትን ያካትታል።
ወታደራዊ ዲሲፕሊን የአየር ኃይሉ የሥራ ባህል መሠረት ነው። ዲሲፕሊን ትዕዛዝን በተገቢው ሁኔታ መፈጸምን፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርን መጠበቅን፣ በቡድን መሥራትንና ለተሰጠ ኃላፊነት ተጠያቂ መሆንን እንደሚጨምር ያነሳሉ፡፡
እነዚህ መርሆዎች በተለይ ፈጣንና ትክክለኛ ውሳኔ በሚያስፈልግባቸው ሁኔታዎች የተግባር ቅንጅትን ለማረጋገጥ ያግዛሉ። በተለይም የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚረዳ የሰው ሃብት፣ ዘመናዊ ትጥቆችና የውጊያ መሰረተ ልማት ለማሟላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
በዚህም የአየር ኃይሉ ተልዕኮውን በተገቢው ሁኔታ እንዲወጣና ከሚያስፈልገው በላይ ኪሳራ እንዳይደርስ የሚያግዙ የሥራ መርሆዎችን ለማጠናከር ይቻላል።
የአየር ክልል ጥበቃ፣ የድንበር ክትትልና ለደህንነት ስጋቶች በወቅቱ ምላሽ መስጠት ተቀናጅተው ሲከናወኑ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚያስፈልገውን የመከላከያ አቅም ያጠናክራሉ።
የአየር ኃይሉ አቅም ሲጠናከር ከውጊያ ውጤት በተጨማሪ የሀገርን የመከላከል አቅም በማሳደግ ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ ይሆናል። የመሣሪያዎች ዘመናዊነት ከሰው ኃይል ብቃት ጋር ሲጣመር የተልዕኮ አፈጻጸምን ለማሻሻልና የሀገርን ደህንነት ለማስጠበቅ ጠንካራ መሠረት ይፈጥራል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

