Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መንግሥት የሰጠው ፈጣን ምላሽና የትግራይ ሕዝብ ድጋፍ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል በሕገወጡ ህወሓት ቡድን የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት የመመለስና በራስ አቅም የሰብዓዊ ድጋፍ በአስቸኳይ የማቅረብ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም የህገወጡን ቡድን ጸረ ሰላምና ጸረ ሕዝብ ድርጊት በማስቆም የሰላምና የልማት ዋልታነቱን በተግባር ባረጋገጠበት ቁርጠኛ ርምጃ የክልሉ ሕዝብ የሰላም አየር እየተነፈሰ ይገኛል፤ ወደ አደባባይ በመውጣትም ለመንግሥት ድጋፉን በመግለጽ ላይ ነው፡፡

መንግሥት የሰጠው ፈጣን ምላሽ የክልሉን ሕዝብ ወደ ሰላማዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እየመለሰ ሲሆን፤ እንደ ባንክና ቴሌኮም የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት ጀምረዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በህገወጡ የህወሓት ቡድን የጥፋት እንቅስቃሴ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የአየር ትራንስፖርት ወደ አገልግሎት የተመለሰ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሳለፍነው እሑድ ጀምሮ ወደ መቀሌ የሚያደርጋቸውን በረራዎች በድጋሚ አስጀምሯል፡፡

ይህም ሕዝቡ ከቦታ ቦታ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ያስቻለ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በክልሉ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን ሥራ ማስጀመሩ በሕብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ እፎይታን የፈጠረ ሆኗል፡፡

በመንግሥት የሰላም፣ የመልሶ ማቋቋም ጥረት በተገኘው አዎንታዊ ውጤት የክልሉ ሕዝብ በተለያዩ ከተሞች ወደ አደባባይ በመውጣት ድጋፉን እየገለጸ ይገኛል፡፡

በቅርቡ በክልሉ ዓዲ ጉዶም ከተማ የተካሄደው ደማቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ሕዝቡ ለፌዴራል መንግሥት የሰላም ጥረቶችና አገልግሎቶችን የመመለስ ርምጃዎች ያለውን ሙሉ ድጋፍ ያሳየበት ነበር።

ከዚህ ባለፈ የትግራይ ሕዝብ በሕገወጡና ቆሞ ቀሩ የህወሓት ቡድን ይደርስበት የነበረውን አፈናና ጭቆና በግልጽ የሚያመላክትና የሰላም አየር መተንፈስ መጀመሩን የሚያሳይ ነው፡፡

መንግሥት በወሰዳቸው ርምጃዎች በክልሉ የባንክና የስልክ አገልግሎቶች መጀመራቸው እንዲሁም ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው መግባት መጀመራቸውን ተከትሎ፤ የክልሉ ነዋሪዎችም መንግሥት የተገኘውን ሰላም እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ከዚህም ባሻገር የመንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሲያከናውናቸው በነበሩ ተግባራት፤ በራስ አቅም የሰብዓዊ ድጋፍን ለዜጎች የማድረስ አቅምን እየገነባ መሆኑ የታየበት ነው።

መንግሥት በክልሉና በሌሎችም አካባቢዎች ፈጣን ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አካባቢዎች በመለየት ድጋፍ የማድረሱ ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በቅርቡም በአላማጣና ሌሎች አካባቢዎች በከባድ ችግርና እንግልት ውስጥ ለነበሩት ወገኖቻችን አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ ተጀምሯል።

በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖና በአካባቢው ባለው ግጭት ምክንያት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የአፋር ክልል ነዋሪዎች ጭምር አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እየተጓጓዘ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

በክልሉ ተቋርጦ የቆየው የትጥቅ ማስፈታት፣ ከታጠቁ ኃይሎች መውጣትና ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስን ያካተተው የዲ.ዲ.አር ሂደትም እንደገና ተጀምሯል።

ከግጭት ወጥተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ የመረጡ ታጣቂዎች የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ማዕከላት እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

የትግራይ ሕዝብ ለረጅም ዓመታት ከነበረበት የሕገወጡ ቡድን ጭቆና ተላቅቆ በአሁኑ ወቅት የሰላም አየር እየተነፈሰ ይገኛል።

መንግሥት ለሕዝቡ የሰላምና የልማት ጥያቄዎች የሰጠው ፈጣን ምላሽና የሕዝቡ አጋርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ አዎንታዊ ውጤቶችን ለማስመዝገብ አስችሏል።

የሀገር ሉዓላዊነትን የማስከበርና የብልጽግና ጉዟዋን አጠናክሮ ለመቀጠል በሚደረገው ርብርብ የሕዝብ ንቁ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ

Exit mobile version