አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰላም የሕዝቦች የነገ ተስፋ፣ የዛሬ ሕይወትና የነጻነት መሠረት ነው።
በትግራይ ክልል በሕገ ወጡ ህወሓት ቡድን አፈና ውስጥ የነበሩ ከተሞች ዳግም የሰላም አየር ሲነፍስባቸው፣ የተቋረጡ አገልግሎቶች ሲጀምሩ፣ ቤተሰቦች ሲገናኙና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ሲነቃቁ የሕዝቡ ተስፋ እየለመለመ መጥቷል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በቅርቡ የታዩ ለውጦች የሕዝቡን ሰላም፣ መረጋጋትና ወደ መደበኛ ኑሮ የመመለስ ጉጉትና ተስፋ በሚገባ አሳይተዋል፡፡
በተለይም በመቐለ የአውሮፕላን በረራ መልሶ መጀመር ከአንድ የትራንስፖርት አገልግሎት ዳግም መመለስ በላይ ትርጉም አለው።
ይህ ለቤተሰቦች መገናኘት፣ ለንግድ ሥራዎች መንቀሳቀስ፣ ለሕክምናና ለሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶች ተደራሽነት መሻሻል እንዲሁም በክልሉና በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል መካከል የተቋረጠውን የአየር ግንኙነት መልሶ ለማገናኘት ያለውን ፋይዳ ያሳያል።
ለረጅም ጊዜ በሕገ ወጡ ቡድን አፈናና ስቃይ ውስጥ የቆየ ማኅበረሰብ ወደ መደበኛ ኑሮው እንዲመለስ የሰብዓዊ ድጋፍ ወሳኝ ሚና አለው።
ምግብ፣ መድኃኒት፣ ንጹሕ ውኃ፣ መጠለያና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ለሕዝቡ በወቅቱ መድረሳቸው ሕይወትን ከመታደግ ባለፈ የመልሶ ማገገም ሒደቱን ያፋጥናል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠው የሰብዓዊ ድጋፍ ፈጣን ምላሽ የሕዝብ አለኝታና መከታ መሆኑን አሳይቷል።
በተለይም መንግሥት በራስ አቅም የሚያከናውናቸው የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች መንግሥት የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የሰብዓዊ እርዳታን በራስ አቅም የማቅረብ ጥረቱ አበረታች ደረጃ መድረሱን የሚያሳዩ ናቸው።
የድጋፍ አቅርቦቱ በተፈለገው መጠንና ጊዜ ለተጎጂዎች መድረሱ፣ በተለይም በአደጋ ውስጥ ላሉ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያንና ሌሎች ተጋላጭ ወገኖች ትኩረት መስጠቱ፣ የሥራውን ውጤታማነት ይወስናል።
ከሰብዓዊ ድጋፍ በተጨማሪ የጤና፣ የትምህርት፣ የመብራት፣ የውኃ፣ የባንክና የመገናኛ አገልግሎቶች መልሰው መሥራት ለክልሉ ማገገም መሠረት ይሆናሉ።
ሕዝቡ ከዕለት ተለት ጭንቀት ወጥቶ ለሥራው፣ ለትምህርቱና ለቤተሰቡ ትኩረት መስጠት የሚችለው እነዚህ አገልግሎቶች በተረጋጋ ሁኔታ ሲቀጥሉ ነው።
ከሰሞኑ በአላማጣ ከተማና በሌሎች አካባቢዎች የተደረገው አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍም መንግሥት ለሕዝብ የሰጠው ምላሽና አለኝታነት ማረጋገጫ ሲሆን÷ ነዋሪዎችም በተደረገላቸው ፈጣን ድጋፍ ይህንኑ አረጋግጠዋል።
በዓዲ ጉዶም እና በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ መንግሥትን የሚደግፉና ሕገ ወጡን ህወሓት የሚቃወሙ ሰልፎችና የሕዝብ ድምፆች ከአስቸጋሪ የአፈና ጊዜ በኋላ የፈነጠቀውን ተስፋ የሚያስተጋቡ ናቸው።
በዚህም ሕዝቡ ቡድኑ ሲያደርስበት የነበረውን በደል፣ ስቃይ፣ የተለያዩ ጫናዎችና ጭቆናዎች፣ እንዲሁም ልጆቹን ለወታደራዊ ግዳጅ ሲጥድበት ከነበረው የዘመናት ስቃይ በመገላገሉ የተሰማውን የእፎይታ እና የደስታ ስሜት በሚገባ አሳይቷል፡፡
ለዘመናት የዚህ እኩይ ቡድን የፖለቲካ ሸቀጥ፣ ማገዶ እና ማስፈራሪያ ሆኖ የቆየው ህዝቡ አሁን ግን ራሱን ከዚህ ቡድን ለመገላገል ያደረገው ጥረት እና ያሳየው እፎይታ፣ የትግራይ ሕዝብ ልማት ወዳድ እና ሰላም ፈላጊ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።
በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም የሚጸናው የሕዝቡ ደኅንነት ሲጠበቅ፣ ሕግ በእኩልነት ሲተገበር፣ የተቋረጡ አገልግሎቶች ሲመለሱና የፖለቲካ ልዩነቶች በውይይት መፍትሔ ሲያገኙ ነው።
በዚህ ሒደት የፌዴራል መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ የክልሉ ማኅበረሰብ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሲቪል ማኅበራትና የሃይማኖት ተቋማት የየራሳቸውን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
የሰላም ፍሬ በተግባር የሚታየው ሕዝቡ ያለ ፍርሃት መንቀሳቀስ፣ ልጆቹን ማስተማር፣ ሥራውን መሥራትና የነገ ዕቅዱን በተስፋ መንደፍ ሲችል ነው።
የትግራይ ሕዝብ የሚገባው በሰላም የመኖር፣ የማደግና የመልሶ ግንባታ ዕድል ነው። ይህ ዕድል በተግባር እንዲረጋገጥ የሁሉም ወገኖች ኃላፊነትና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል።

