አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)አዲስ አበባ ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት መሆን ጀምራለች አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አመራር ኢኒሼቲቭ የ2026 የአመራሮች ፎረም በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ነው፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ይህ መድረክ ልምድ ለመለዋወጥ፣ እርስ በርስ ለመማማርና ከተማችን እያካሄደች ያለውን የለውጥ ጉዞ ለማካፈል ጠቃሚ ዕድል ፈጥሯል።
የአዲስ አበባ የለውጥ ጉዞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርቆ አሳቢነትና ለከተማዋ ባስቀመጡት ርዕይ የተቃኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ርዕይ ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤቶች እየቀየርን ነው ብለዋል።
በትራንስፖርት፣ በቤቶች ልማት፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አገልግሎቶችና በትውልድ ግንባታ ላይ በምናከናውናቸው ሥራዎች የነዋሪዎቻችንን ተጠቃሚነት እያረጋገጥን ነው ሲሉም አስረድተዋል።
በራሳችን የፋይናንስና የዕውቀት አቅም ላይ ተመሥርተን በመሥራታችን፣ የአዲስ አበባ ተሞክሮ ለሌሎች የአፍሪካና የዓለም ከተሞች ጠቃሚ ትምህርቶችን እያበረከተና አዳዲስ የልማት ዕድሎችን እያመላከተ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ አበባን በአፍሪካ ህጻናትን ለማሳደግ ምርጥ ከተማ ለማድረግ ያለንን ጽኑ ቁርጠኝነት እያሳየን ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ በሕጻናት እድገት ላይ ያተኮሩ ተግባራትን በማጠናከር፣ የሕጻናትን ደህንነት፣ ትምህርትና የወደፊት ሕይወት በከተማችን የልማት አጀንዳ ማዕከል ላይ አስቀምጠናል ብለዋል።
ከየአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አመራር ኢኒሼቲቭ መሪዎችና የፎረሙ ተሳታፊዎች ጋር በመሆን፣ በመዲናዋ በልዩ ሁኔታ የተገነባውንና ለፕሮግራሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባደረገችው ሊዛ ዲዬጎ መታሰቢያ የተሰየመውን የሕጻናት እንክብካቤ ማዕከል መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡
ለዚህ መርሐ ግብር ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

