አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአርበኞች ሀገር ናት፤ አርበኝነት ዋጋ ለሚገባው ነገር ዋጋ መክፈል ነው፤ ኢትዮጵያውያን አባቶች ጠላትን በትብብር መንፈስ ድል ነስተው ነጻነት ያላት ሉዓላዊነት ሀገር በደም አጽንተው አስረክበዋል፡፡
በታሪክ በተካሄዱ መርህ አልባ ውሳኔዎች የተነሳ ኢትጵያ የባሕር በር አልባ ሆና ለበርካታ ዓመታት ዘልቃለች፡፡ ነገር ግን እውነት ወቅቱን ጠብቆ መታየቱ ፍትሕም ሊሰፍን የተገባ ነውና ጊዜውን ጠብቆ ጥያቄው ተነስቷል፡፡
ሀገርን ከጠላት መጠበቅ፣ ሊወር የመጣን ድል ነስቶ መመለስ የትናንት አባቶቻችን የአርበኝነት መገለጫ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ሀገር ኢኮሚዋን ማሻሻል፣ ዜጎቿ የምግብ ሉዓላዊነታቸው እንዲጠበቅ፣ የቴክኖሎጂ አቅሟ እንዲጎለብት፣ ደህንነቷ እንዲጠበቅ ትሻለች፤ የባሕር በር ይህን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊየን ህዝብ በላይ የያዘችው ኢትዮጵያ ታሪክም፣ ዓለም አቀፍ ህግም የሚደግፋትን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ማንሳቷ ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም፡፡
ይልቁንም የሌሎች ሀገራት ወደቦችን ለመጠቀም የምታወጣው ወጪ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለዜጎች የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን የሚገነባ፣ ለወጣቶች የስራ ዕድልን የሚፈጥር፣ የኑሮ ውድነትን የሚያስተካል በመሆኑ ይህ የኢኮኖሚም ጥያቄ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅሟን ለማሳደግ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እየሰራች፣ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እየተጋች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያውያን አርበኝነትን በቃል ብቻ ሳይሆን፤ በተግባር ማሳየት መገለጫችን ነው፤ የአባቶችን ጀግንነት የወረሰ ትውልድ ደግሞ ዛሬም ይህን ለማስቀጠል ይተጋል፡፡
ትውልዱ የባሕር በር ጥያቄ ማለት የሉዓላዊነት ጥያቄ መሆኑን ይረዳል፤ ዘመኑን በዋጀ መንገድም የአርበኝነት መንፈሳቸውን ያስቀጥላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርበኝነት ለሀገር የሚከፈል ከራስ ወዳድነት የነጻ መሥዋዕትነት ነው ብለዋል፡፡
ሀገር መውደድ፣ ከራስ ወዳድነት መውጣትን፣ ከራስ በላይ ዋጋ መክፈልን ይሻል፤ ሀገር ከሚገባት ከፍታ ላይ እንድትገኝ መስራትን ይፈልጋል፡፡
ትናንት አባቶች ደምና አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩልንን ሀገር በተገቢው መንገድ ካላስረከብን በታሪክ ሚዛን ስንመዘን የሚያኮራ ሳይሆን የሚያሳፍረን ይሆናል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ በድህነት ስሟ እንዳይነሳ ኢኮኖሚዋን አጠንክረን፣ ፍትህን አስጠብቀን፣ የተከበረችና የታፈረች ኢትዮጵያን ለትውልድ እንድናወርሳት በመሻት የባሕር በር ባለቤትነት መብታችንን ማስከበራችን የእኛ ትውልድ የህልውናን ማስከበሪያና የአርበኝነት መገለጫ ነው፡፡
በቤተልሔም ግርማ

