Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ደፍቃለች!

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት፣ 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በታሪኳ ማዕበል ያልተፈራረቀባት፣ ሴራ ያልተሸረበባት የጊዜ ምዕራፍ የላትም። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በፈተናዎች እቶን ውስጥ አልፋ ይበልጥ ደምቃ እና ጠንክራ የምትወጣ ድንቅ ሀገር ነች።
ዛሬም ታሪክ ራሱን ደግሟል፤ ከውስጥም ከውጪም ኢትዮጵያን ለመጣልና ለማንበርከክ የሞከሩ ኃይሎች ሁሉ የሽንፈትን ማቅ ለብሰው አፍረዋል።
ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ እና በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ ፈጽሞ እንደማትደራደር በተግባር አሳይታለች። በተለይም የሁለቱ ታላላቅ ውኃዎች የዓባይ ወንዝ እና የቀይ ባህር ተደራሽነት የሀገሪቱ የህልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ሆነዋል።
የውጭ ኃይሎች እነዚህን የተፈጥሮ ፀጋዎች በመጠቀም ሀገሪቱን ለመቆለፍ እና በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ለመጠቅለል የከፈቱት ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ዘመቻ ከሽፏል። ኢትዮጵያ በፅኑ አቋሟ የጥቅሟን መከበርና የአካባቢው የኃይል ሚዛን መሪነቷን አስመስክራለች።
ለሀገር ህልውና መከበር ግንባር ቀደም ዋጋ የከፈለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው። ሠራዊቱ ባሳየው ወደር የለሽ ጀግንነት፣ ቁርጠኝነት እና ስትራቴጂካዊ ጥበብ የሀገርን አንድነት ለመናድ የመጣውን ጠላት ሁሉ ደፍቋል።
ከባዕዳን ኃይሎች ጋር በማበር የሀገርን ሉዓላዊነት አሳልፈው ለመስጠት የሞከሩ የውስጥ ባንዳዎችና ከሀዲዎች ምሽጋቸው ፈርሶ እንዲሯሯጡ ተደርገዋል።
በተለይም ሕገ ወጡ የህውሓት ቡድን የኢትዮጵያን ክንድ መቋቋም አቅቶት፤ ሀገርን የማፍረስ ህልሙ መክኖ፤ ዛሬ ወደ ላኪዎቹና ወደ ጌቶቹ ጉያ ለመሾግጥ ተገድዷል። ይህ ድል የሴራ ፖለቲካ እና የውክልና ጦርነት በኢትዮጵያ ምድር ፈጽሞ እንደማያሸንፍ ግልጽ ማሳያ ነው።
ደግሞ ታሪክ ምስክር ነው፤ ኢትዮጵያን የነኩ ሁሉ ውድቀትን ተከናንበዋል። ሀገሪቱ ዛሬም ጠላቶቿን እያንበረከከች፣ ሴራዎችን እያከሸፈች እና አዳዲስ የድል ታሪኮችን እየጻፈች ወደፊት ትጓዛለች።
የኢትዮጵያ ትንሳኤ በጠላቶቿ መቃብር ላይ የሚገነባ መሆኑ በተግባር የታየ ሲሆን ይህ ትውልድም የጀግኖችን አደራ በመቀበል ሀገሩን በልማት፣ በዲፕሎማሲና በሉዓላዊነት ከፍታ ላይ የማቆየት ታሪካዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነት እና በጀግኖቿ ክንድ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች!
በኃይለኢየሱስ መኮንን
Exit mobile version