አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ያካሄደችው መዋቅራዊ ሽግግር የሀገሪቱን የምርት እድገት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
ግብርናን ከባህላዊ የዕለት ጉርስ ፍለጋ አውጥቶ ወደ ዘመናዊ፣ ምርታማ እና ኢኮኖሚን ወደሚመራ የሃብት ምንጭነት ለመቀየር የተሄደበት ርቀት የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፎ የልማት ምሳሌ የሚያደርግ ስኬት እየተመዘገበበት ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ደጋግመው በአፅንኦት እንደተናገሩት “ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን በራሷ አቅም ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፤ ምርቷን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ቀጣናዊና አህጉራዊ የምግብ አቅርቦት ማዕከል የመሆን ሙሉ አቅም አላት”፡፡
ይህ ሀሳብ በተግባር መሬት በመርገጡም ሀገሪቷ ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ታሪካዊ የሚባሉ ስኬቶችን ለማስመዝገብ በቅታለች።
የግብርና ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው የ2018 በጀት ዓመት መረጃ መሠረት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ33 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ1 ነጥብ 85 ቢሊየን ኩንታል በላይ አጠቃላይ የግብርና ምርት መሰብሰብ ተችሏል።
ይህ ስኬት ከቀደመው የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር የ280 ሚሊየን ኩንታል ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም በሀገሪቱ የግብርና ታሪክ ውስጥ የታየ ትልቅ የእድገት ማረጋገጫ ነው።
ለዚህ ታላቅ ስኬት ደግሞ በኢትዮጵያ የሰብል ማምረቻ ወቅቶች ውስጥ ዋነኛው የሆነው የመኸር እርሻ የአንበሳውን ድርሻ ይዟል። መኸር የሀገሪቱን የምግብ ፍላጎት ከመሸፈንም በላይ፤ የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎችን በማቅረብ እና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ይህን የተገኘውን ስኬትና የእድገት ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል በያዝነው 2019 በጀት ዓመት የበለጠ ሰፊና ስትራቴጂካዊ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል።
በግብርና ሚኒስቴር መረጃ መሰረት በያዝነው ዓመት የመኸር እርሻ በአጠቃላይ 22 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማልማት ከ730 ሚሊየን ኩንታል በላይ የመኸር ምርት ለማግኘት ታቅዷል።
የመኸር እርሻ ዛሬ በኢትዮጵያ የዕለት ጉርስን የመሸፈን ተግባር ብቻ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት ግብርና የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ነጻነት መሠረት ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ አልፎ ለገበያ የሚያቀርበውን ምርት በማሳደግ የገቢ ምንጩን እንዲያጎለብትና ሀብት እንዲያከማች የሚያስችል ነው።
ቀደም ሲል ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይገቡ የነበሩ እንደ ስንዴ ያሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ በመተካት ሀገር በቀል ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉ የግብርናው ዘርፍ ትኩረት የምግብ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ በግልፅ ያመላክታል፡፡
ይህ “ከምግብ ባሻገር” የሆነው የአስተሳሰብና የአሰራር ሽግግር ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥን፣ የምግብ ዋስትናዋን በዘላቂነት የሚያረጋግጥ እና ሀገሪቱን በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚና የምግብ ዋስትና መሪ የሚያደርጋት ትልቅ የለውጥ ምዕራፍ ነው።
በታሪኩ ለገሰ

