አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲጂታል አካታችነትን በማጎልበት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በትኩረት ይሰራል አሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ፍሬሕይወት ታምሩ።
ፍሬሕይወት ታምሩ ከሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት አመራሮች ጋር በቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በአዲሱ የኢትዮጵያ ግራንድ ስትራቴጂ ለዘርፉ ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባር አኳያ የወደፊት ራዕይን ለመተግበር በቁርጠኝነት ይሰራል፡፡
ዲጂታላይዜሽንን በሚፈለገው ግብና ፍጥነት መተግበር እንዲቻል ለአጠቃላይ ዘርፉ አስቻይ ምሕዳር መፍጠር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በቀጣይ በዘርፉ ያሉ አቅሞችን በመለየት ተልዕኮዎችን ለማሳካት መደጋገፍና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ከማነቃቃት አንጻር ትልቅ ለውጥ እንደምናመጣ እምነት አለኝ ሲሉም ገልጸዋል ሚኒስትሯ፡፡
የዲጂታል አካታችነትን በማጎልበት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማስገንዘባቸውንም ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

