አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀይ ባህር ለአፍሪካ ቀንድ በተለይም ለኢትዮጵያ ሰፊ የጨው ውሃ ሳይሆን ለዘመናት የታሪክ ትንፋሽ እና የንግድ መስመር ሆኖ የኖረ ሕያው ምስክር ነው።
የቀይ ባህር እና የኢትዮጵያ ታሪክ የታሰረበት ገመድ ከተራ የወደብ ጥያቄ የተሻገረ እጅግ ጥልቅ የሆነ የታሪክ እና የስነ-ልቦና ትስስር አለው።
የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ እና ዓለም አቀፍ የጂኦሎጂ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቀይ ባህር የተፈጠረው ከአረቢያ እና ከአፍሪካ ሰሌዳዎች መራራቅ የተነሳ የምድር ቅርፊት ሲሰነጠቅ ነው።
ይህ የምድር ስንጥቅ በሰሜን በኩል ቀይ ባህርን ሲፈጥር፣ በደቡብ በኩል ደግሞ ቀጥ ብሎ ወደ ምስራቅ አፍሪካ በመዘርጋት የታላቁ የምድር ስምጥ ሸለቆ ሆኖ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ልብ ዘልቋል።
የቀይ ባህር ማዕበል እና የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆዎች የተሰሩት ከአንዱ የምድር ቅርፊት ስፌት በመሆኑ፣ የአፋር በረሃ (ዳሎል) የቀይ ባህር ታናሽ ወንድም ነው ማለት የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም።
ቀይ ባህር በሩቅ የሚታይ የውሃ አካል ሳይሆን በኢትዮጵያ መሬት አካል ውስጥ የተዘረጋ የታሪክና የተፈጥሮ ዐሻራ ነው።
ይህ የተፈጥሮ ቁርኝት በታሪክ መድረክ ላይም ህያው ሆኖ ይታያል። የአክሱም ሥልጣኔ በዓለም መድረክ ላይ በግዙፍነት በቆመበት ዘመን የአዱሊስ ወደብ የቀይ ባህር የንግድ እምብርት ነበር።
ከሮም፣ ከህንድ እና ከግሪክ የሚመጡ መርከቦች ቀይ ባህርን አቋርጠው አዱሊስ ሲደርሱ፣ የሚያገኙት የንግድ ትስስር ብቻ አልነበረም፤ የኢትዮጵያን ስልጣኔ ጥበብና ክብር ጭምር እንጂ።
ቀይ ባህር በራሱ ጨዋማ በመሆኑ፤ በባህሩ ዳርቻ ያሉ የንግድ ማዕከላት በሙሉ ህይወታቸውን ለማስቀጠል የሚያስፈልጋቸውን የንጹህ ውሃ፣ የእህል እና የቁሳቁስ አቅርቦት የሚያገኙት ከኢትዮጵያ ከፍታማ ተራሮች በሚወርዱ ወንዞች ነበር።
ባህሩ የውጭውን ዓለም ወደ ኢትዮጵያ ሲጋብዝ፣ የኢትዮጵያ ተራሮች ደግሞ ለባህሩ ዳርቻዎች ሕይወትን ሰጥተዋል።
ይህ የውሃ እና የታሪክ ትስስር ደግሞ ከዓባይ ወንዝ ጋር ይበልጥ የተሳሰረ ነው።
ኢትዮጵያ የዓባይ ምንጭ እና የቀይ ባህር ደጀን ናት። ቀይ ባህር እና ዓባይ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካ ውስጥ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።
የዓባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ተራሮች ተነስቶ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ሲፈስ፣ የኢትዮጵያ የንግድና የደህንነት መስመር ደግሞ በቀይ ባህር በኩል ወደ ዓለም ይዘረጋል።
በቀይ ባህር አካባቢ የሚፈጠረው ማናቸውም የፖለቲካ እና የደህንነት መናወጽ፣ በቀጥታ በዓባይ ተፋሰስ እና በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ የምታደርገው ልማትና የምታሳየው የኢኮኖሚ እድገት ቀይ ባህርን ለሚሻገሩ የዓለም የንግድ መርከቦች አስተማማኝ ዋስትና ነው።
በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የባህር በር ሳታገኝ በምትቆይበት ጊዜም እንኳ የቀይ ባህር፣ የዓባይ እና የኢትዮጵያ ትስስር ፈጽሞ አልተበጠሰም።
የቀይ ባህር የፀጥታ ሁኔታ፣ የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ እና የጂኦፖለቲካ ማዕበል ሁልጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያን በር ያንኳኳል።
ኢትዮጵያ ለቀይ ባህር ቅርብ የሆነች፣ ሰፊ የህዝብ ቁጥር እና እያደገ የመጣ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር በመሆኗ፣ ያለ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር የንግድ መስመር ሙሉ ደህንነት ሊኖረው አይችልም።
ዓባይ የኢትዮጵያ የህይወት የደም ስር እንደሆነው ሁሉ፣ ቀይ ባህርም የውጭ መተንፈሻዋ ነው።
ስለሆነም ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ የሩቅ ህልም ሳይሆን፤ የታሪክ ሃቅ እና የነገ ተስፋ ነው። ወደቦች የድንበር በሮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ የባህር በር ግን ለኢትዮጵያ የተፈጥሮ፣ የታሪክ ሃቅ እና የሕልውና ባለቤትነት ጥያቄ ነው።
በሶስና አለማየሁ

