አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ ከተማ በአሜሪካ ፣ ላስ ቬጋስ ፣ ኔቫዳ በተዘጋጀው “IMEX America 2026” የማይስ ቱሪዝም ኤክስፖ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈች ነው።
በኤክስፖው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የቱሪዝም ኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የቱሪዝም ሀብቶች እና አዳዲስ የመሰረተ ልማት ዝግጅቶችን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል።
ከ150 በላይ ከሚሆኑ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ከ3 ሺህ 700 በላይ ተሳታፊ ድርጅቶችና ኩባንያዎች የተገኙ ሲሆን አዲስ አበባ በኤክስፖው መሳተፏ በዘርፉ ያላትን ተወዳዳሪነት የሚያጎለብት እንደሆነ የከተማዋ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።
አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችንና ኮንፈረንሶችን በብቃት በማስተናገድ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን አስመስክራለች።
ይህ ኤክስፖ ከተማዋ ያላትን የቱሪዝም ጸጋዎች ይበልጥ ለማስተዋወቅና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዘርፉ ዋና ዋና ተዋናዮች፣ አስጎብኚዎችና ባለሃብቶች ጋር ጠንካራ የንግድ ትስስር ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረው ይሆናል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

