አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የተቋማትን የአፈጻጸም አቅም ለማጠናከር የዲጂታል ሥርዓቶችን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው አለ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት።
ኢንስቲትዩቱ በየዓመቱ ጥቅምት 4 ቀን የሚከበረውን የዓለም ደረጃዎች ቀን አስመልክቶ ከአምራቾች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ(ዶ/ር) በዚሁ እንደገለጹት ፥ የደረጃዎችና የጥራት ሥርዓትን ማጠናከር ለዘላቂ ልማት፣ ለሀብት ቆጣቢነት፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለዜጎች ጥቅም ያለው አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው።
ኢንስቲትዩቱ ሀገራዊ ደረጃዎችን ከማዘጋጀት ባሻገር የምርቶችና የአገልግሎቶች ጥራት እንዲሻሻል የሥልጠና እና የቴክኒክ ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝና የዛሬው መድረክም ለሕብረተሰቡ ለማስገንዘብ፣ ልምዶችን ለመለዋወጥና በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመወያየት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ተቋሙ የደረጃዎችን አጠቃቀም ለማስፋፋት፣ የተቋማትን የቴክኒክና የአፈጻጸም አቅም ለማጠናከር እንዲሁም አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂና በዲጂታል ሥርዓቶች የበለጠ ተደራሽና ቀልጣፋ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ በየተቋማቱ የሚከናወኑ ሥራዎች የመጨረሻ ዓላማ ለዜጎች ጥቅም ማምጣት ነው ብለው የሚከናወኑ ተግባራት በዜጎች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት ሲችሉ ብቻ ውጤታማ ሊባሉ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።
የደረጃዎችና የጥራት ሥርዓትን ማጠናከር የሀገርን የምርትና የአገልግሎት ጥራት ከማሻሻል ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለዘላቂ ልማት የጎላ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የዓለም ደረጃዎች ቀን በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር ሲሆን፤ የዘንድሮው መሪ ቃል “ንፁህ እና አዋጭነት ያለው ኢነርጂ” የሚል ነው።
በዮሐንስ በቀለ

