አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የኤርትራ ሕዝብ ስጋት ሆኖ አያውቅም አለ የኤርትራ ሠማያዊ ማዕበል።
የኤርትራ ሠማያዊ ማዕበል የዲፕሎማሲ ኃላፊ ዮኤል ዮሀንስ ፥ ለ35 ዓመታት ኤርትራን የግል እስር ቤት ያደረገው የኢሳያስ አፈወርቂ ሥርዓት የኢትዮጵያን የአብሮ መልማት ጥያቄ ጥላሸት ለመቀባት የሚሄድበት መንገድ የኤርትራ ሕዝብ አቋም እንዳልሆነ አንስተዋል።
የኤርትራ ሕዝብ ልማትና ፍትሕ የናፈቀው በመሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመልማት ፍላጎት ያለው ቢሆንም በአምባገነናዊው ሥርዓት ግን ይህ ፍላጎቱ ሲጨናገፍ እንደኖረ ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ ለኤርትራ ስጋት ሆና አታውቅም ያሉት አቶ ዮኤል ዮሐንስ÷ ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ተጠቃሚነት ጥያቄ ለኤርትራዊያን የአብሮ ማደግ እድል እንጂ እንደ ስጋት የሚታይ አይደለም ብለዋል።
በአስመራ የሚገኘው የአዛውንቶች ስብስብ ግን ከካይሮ ተልዕኮ እየተቀበለ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ጥያቄ ለማጨናገፍ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የኤርትራዊያን የደኅንነት ዋስትና እንጂ ስጋት አለመሆኗን በመላው ዓለም የሚገኙ ኤርትራዊያን እንደሚረዱ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሞሊቶ ኤልያስ

