አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም(አይ ኤም ኤፍ) ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ሊያጠናክር ይገባል አሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፡፡
የአፍሪካ ብሔራዊ ባንክ ገዥዎች ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ጋር በባንኮክ ተወያይተዋል፡፡
በመድረኩ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ÷በኢትዮጵያ የተደረገው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማረጋጋት መቻሉን እንዲሁም አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችን እየከፈተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ታዳጊ የአፍሪካ ሀገራት የማይበገር ኢኮኖሚ እንዲገነቡ ለማስቻል ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አጋርነቶችን እና ጥልቅ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ብሔራዊ ባንክ ገዥዎች በበኩላቸው ÷በመዋቅራዊ ማሻሻያዎች፣በፈጠራ እና በቀጣናዊ ውህደት አማካኝነት የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ አቅም ወደ ዘላቂ ዕድገት ለመለወጥ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያ የአፍሪካ የባንክ ገዥዎች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካ ታላላቅ የልማት ፕሮጄቶችን በፋይናንስ እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረባቸውን የብሔራዊ ባንክ መረጃ አመላክቷል፡፡

