Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዘመኑን ያልዋጀው የግብፅ “የእኔ ብቻ” ቅዠት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የታላቁ ዓባይ ወንዝ የተፈጥሮ ጸጋ በምስራቅ አፍሪካ እና በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የዘለቄታ ሰላም፣ ልማት እና የጋራ እድገት ትልቁ ማስተሳሰሪያ ሊሆን ቢገባውም ግብፅ በዓባይ ተፋሰስና በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ላይ ስትከተለው የኖረችው መርህ-አልባ ፖሊሲ፣ ከታሪካዊ የወረራ ሙከራዎች ጀምሮ እስከ ዘመናዊው የደህንነትና የዲፕሎማሲ ደባዎች ድረስ የተዘረጋው የፖለቲካ ግፍ አፍሪካን ቀና እንዳትል አድርጓታል።
የግብፅ ወረራ ፍላጎት የቅርብ ጊዜ ክስተት አይደለም። በ19ኛው ክፍለ ዘመን በፈረንጆቹ 1875 እና 1876 የግብጹ ኸዲቭ ኢስማኢል ፓሻ የዓባይን ምንጭ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ወደ ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የወረራ ጦርነቶችን አውጇል።
ሆኖም ግን የግብፅ ገዢዎች ያላሰቡትና ያልጠበቁት ጽኑ የአፍሪካውያን መከላከል ገጥሟቸዋል፤ በጀግኖች የኢትዮጵያ አባቶች የተቀናጀ መከታ የወራሪው ጦር በጉንድት እና በጉራዕ ጦርነቶች በታሪካዊ ሽንፈት ድል ተመትቶ ተመልሷል።
ከኢትዮጵያ ባሻገር፣ ግብፅ ጎረቤት ሱዳንን በመውረር ለረጅም ጊዜያት በቅኝ ግዛትና “በጋራ አስተዳደር” ስም የሱዳንን ህዝብ ሰብዓዊ መብት በመርገጥ፣ የተፈጥሮ ሀብቷን ስትበዘብዝ እና ሀገራዊ ማንነቷን ስታደክም ቆይታለች።
ይህ ታሪካዊ እውነታ የሚያሳየው ግብፅ ለአፍሪካውያን ጎረቤቶቿ ያላት ዕይታ የጋራ ተጠቃሚነት ሳይሆን የበላይነት እና የብዝበዛ መሆኑን ነው።
ግብፅ ከአፍሪካ ሀገራት ፍላጎትና መብት ውጪ የዓባይን ውኃ ለብቻዋ ለመጠቅለል ስትል በእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ጥላ ስር የተሰሩ ሕገ-ወጥ ስምምነቶችን እንደ ብቸኛ ሕግ በመቁጠር አፍሪካውያን በራሳቸው ሀብት እንዳይጠቀሙ ስታደርግ ቆይታለች።
የ1929 ስምምነት እንግሊዝ ከራሷ ጥቅምና ከግብፅ ጋር ብቻ ያደረገችው የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትን መብት ሙሉ በሙሉ የካደ ውል ነበር።
የ1959 ስምምነትም ግብፅ ከሱዳን ጋር ብቻ ተፈራርማ የዓባይን ውኃ ሙሉ በሙሉ ለሁለቱ ሀገራት ብቻ የተካፈለችበት፣ የውሃው ዋና ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያን እና ሌሎች የተፋሰሱን ሀገራት ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ ፈጽሞ ያገለለ በደል ነው።
በእነዚህ ፍትኃዊ ባልሆኑ ስምምነቶች ስም ግብፅ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ህዝቦቻቸውን ከድህነት ለማውጣት የሚያደርጉትን ማንኛውንም የልማት እንቅስቃሴ የማገድ መብት አለኝ በማለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ጫና ስታደርግ ቆይታለች።
ለዚህም ትልቁ ማሳያ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የልማት ፕሮጀክቶችን እንዳትገነባ ከዓለም ባንክ እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ ያደረገችበት የቅርብ ጊዜ ተንኮል ነው።
በልማት መስክ የሚደረጉ እገዳዎች ብቻቸውን ግብፅን አላረኳትም። የአፍሪካ ሀገራት በራሳቸው እግር እንዳይቆሙና ከድህነት እንዳይወጡ ለማድረግ አካባቢውን በሽብርና በእርስ በእርስ ግጭት የማተራመስ ስልት ስትከተል ኖራለች።
በተለይም የኢትዮጵያን የውስጥ አንድነት ለማላላትና የልማት ትኩረቷን ለማስቀየር የውስጥ አማጺያንን እና ተገንጣይ ቡድኖችን በገንዘብና በደህንነት መዋቅር መደገፍ፣ የጎሳና የብሔር ግጭቶች እንዲባባሱ ማድረግ፣ በምስራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ጥርጣሬና ጦርነት እንዲነግስ የፖለቲካ ደባዎችን መሸረብ ዋነኛ መሳሪያዎቿ ነበሩ።
ይህ የደባ ፖሊሲ ዛሬም ቢሆን አልቆመም፤ ቅርጹን ቀይሮ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ዛሬም ግብፅ በሱዳን የውስጥ ጉዳይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ጣልቃ በመግባት፣ ሱዳናውያንን በአየር ድብደባ በመምታትና ወንድማማች ህዝቦችን እርስ በእርስ በማባላት የሀገሪቱን ሀብት ለመቀራመት አበክራ እየሰራች ትገኛለች።
በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን የውስጥ አለመረጋጋት ለማስቀጠል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በመመደብ በኤርትራ እና በሱዳን አቅጣጫዎች በኩል ለታጣቂዎች የጦር መሳሪያና የገንዘብ ድጋፍ በማቅረብ ቀጣናውን ወደ አዲስ የጦርነት አዙሪት ለማስገባት ጥረት እያደረገች ነው፡፡
ግብፅ በምስራቅ አፍሪካ ላይ የምትከተለው የ”እኔ ብቻ ልኑር” ፖሊሲ ጊዜው ያለፈበት እና የአፍሪካን አህጉራዊ አንድነት የሚቃወም ነው።
አፍሪካውያን በራሳቸው ሀብት የመጠቀም፣ ህዝቦቻቸውን ከድህነት የመታደግ እና ሉዓላዊነታቸውን የማስከበር ተፈጥሯዊ መብታቸውን በምንም ዓይነት የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ ወይም የወታደራዊ ደባ ሊያጡት አይገባም።
የታሪክ እውነታ እንደሚያስተምረን የአፍሪካውያን የጋራ ጥረትና ጽናት የግብፅን የዘመናት ደባ አክሽፎ ፍትሃዊ የጋራ እድገትን ማረጋገጡ አይቀሬ ነው።
በታሪኩ ለገሰ
Exit mobile version