Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዳንጎቴ ግሩፕ አክሲዮን ሽያጭ በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ መቅረቡ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት በር ይከፍታል – አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዳንጎቴ ግሩፕ አክሲዮን ሽያጭ በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በኩል መቅረቡ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት በር የሚከፍት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ።

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ከናይጄሪያው ግዙፍ ኩባንያ ዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአክሲዮን ሽያጭ ማስተዋወቂያ መድረክ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል በይፋ ተጀምሯል።

አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፥  የዳንጎቴ ግሩፕ የአክሲዮን ሽያጭ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ብቁ ባለሀብቶች መቅረቡ ገና ለጋ ለሆነው የሀገሪቱ የፋይናንስ ገበያ ትልቅ ዕድገትና ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

ይህ ክስተት በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠራቸውን ዕድሎች እና የአፍሪካ ባለሀብቶች ከሀገር ድንበር ተሻግረው ለመሳተፍ ያላቸውን እያደገ የመጣ አቅም የሚያሳይ መሆኑንም አብራርተዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚረጋገጠው የአህጉሪቱን ቁጠባ ለአፍሪካ ኩባንያዎች በማዋል፣ ድንበር ተሻጋሪ ኢንቨስትመንትንና የኢኮኖሚ ውህደትን በማጠናከር እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የዳንጎቴ ግሩፕ በኢነርጂ፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች ያደረጋቸው ኢንቨስትመንቶችም የዚህ አህጉራዊ አቅም ማረጋገጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የዳንጎቴ ግሩፕ መስራችና ባለቤት አሊኮ ዳንጎቴ በበኩላቸው ኩባንያቸው በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት ፍላጎት ገደብ የሌለውና አጋርነቱም ዘላቂ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ዳንጎቴ ግሩፕ ‘ራዕይ 2030’ን ለማሳካት የሚያደርገውን ኢንቨስትመንት ወደ 50 ቢሊየን ዶላር ማሳደጉንና ከዚህ ውስጥ 10 በመቶውን ለኢትዮጵያ መደቡን ተናግረዋል።

ዳንጎቴ ግሩፕ በኢትዮጵያ በነዳጅ፣ ማዳበሪያና ሌሎች ዘርፎች የ5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት አለው ብለው ከሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ቢያንስ 10 በመቶ ድርሻን በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በኩል ለአክሲዮን ሽያጭ እንደሚያቀርብም ጠቁመዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በሰዓዳ ጌታቸው

Exit mobile version