Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከጀግኖች መስዋዕትነት እስከ ዘመናዊው የሥልጣኔ ጉዞ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የሚለውን ታላቅ ስም ስናነሳ በቅድሚያ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው የማይበገር ሀገራዊ ህልውና፤ የሺህ ዓመታት የሉዓላዊነት እና የስልጣኔ ታሪክ ነው።
ነገር ግን ይህንን የሀገረ መንግሥት ከፍታና ዘላቂነት ያለ አስተማማኝ እና ጽኑ የደህንነት መሠረት ማሰብ አይቻልም።
የሀገር ሁለንተናዊ እድገት፣ ብልጽግና እና ሰላም እውን ይሆኑ ዘንድ ሌት ተቀን በብርድና በበርሃ ወጥተው ለሚያድሩት፣ ዳር ድንበር እና ሰላምን አስከብረው በተጠንቀቅ ለሚቆሙት ብርቱ የጸጥታ ኃይሎቻችን ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ጸንታ እንድትቆም፤ ሉዓላዊነቷም ሳይደፈር ለትውልድ እንዲሸጋገር የተከፈለው እንዲሁም እየተከፈለ ያለው ዋጋ ቀላል አልነበረም፤ አይደለምም።
ዛሬ ላይ ቆመን ስለ ነገይቷ ኢትዮጵያ ከፍታ ስናስብ የእነዚህን የሀገር አለኝቶች በደምና አጥንት የተከፈለ መስዋዕትነት መሠረት በማድረግ መሆኑንም መዘንጋት አይገባም።
ይህንን መስዋዕትነት በመዘከርና ክብርን በመስጠት፤ ኢትዮጵያ አዲስ ታሪካዊ የስልጣኔና የከፍታ ምዕራፍን በመክፈት ላይ ትገኛለች።
የነበራትን የስልጣኔና የኃያልነት ታሪክ ዘመናዊውን ዓለም በሚዋጅ መልኩ በራስ አቅም ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ፍሬዎችን ማፍራት ጀምሯል።
ኢትዮጵያ በራሷ የሰው ኃይል፣ ዕውቀት፣ በልጆቿ ፈጠራና በራሷ አቅም የመከላከያ አቅሟን ማዘመን ችላለች፡፡
የራሷን የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ አቅም ጊዜውን በሚመጥን አየር ኃይል፣ ተዋጊ አውሮፕላኖችንና ዘመናዊ ሰው አልባ ቴክኖሎጂዎችን (ድሮኖችን) በመጠቀም የአየር ላይ የመከላከልና የመቆጣጠር አቅሟን አሳድጋለች።
በሀገር ውስጥ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱ የታጠቁ ተሸከርካሪዎችን፣ ጥገኝነትን የሚያስቀሩ እንደ ተተኳሽና ከባድ መሳሪያዎችን በማምረት ራስን ችሎ የመቆም ምሳሌነቷን አጉልታ ማሳየት ችላለች፡፡
ይህ ወታደራዊ የማምረት አቅምና የቴክኖሎጂ ሽግግር፤ የመከላከያ ተቋማትን ማጠናከር ብቻ አይደለም፤ የሀገርን ኢኮኖሚ እና ሰላም በጽኑ መሠረት ላይ የመገንባት ርምጃ እንጂ።
ኢትዮጵያ ጀግኖቿ መስዋዕትነትን ከፍለው ያኖሩትን የጥንት ስልጣኔ እና የኃያልነት ታሪክ እንደገና አድሳ ወደፊት ለማስቀጠል የምታደርገው ጉዞ በከፍተኛ ፍጥነት እየገሰገሰ ይገኛል።
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version