Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ አየር ክልል ዘብና የድል አርማ፡ የሰማዩ ንስር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስከበር ዘመኑን የዋጀና የተሟላ አቅም ያለው አየር ኃይል መገንባት ከቀዳሚ ብሔራዊ ተግባራት አንዱ ነው።
አየር ኃይል የአንድን ሀገር የአየር ክልል በንስር ዐይን እየቃኘ ከማንኛውም የውጭ ጥቃት የመጠበቅ እና የሀገሪቱን ሰማይ በተጠንቀቅ የመጠበቅ ኃላፊነት ይወጣል።
ጥቃት ቢፈጸምም አስፈላጊውን አጸፋዊ ርምጃ በመውሰድ ጥቃቱን የመቀልበስ፣ በፍጥነት የመመከትና ኪሳራን የመቀነስ ብቃት ሊኖረው ይገባል።
ይህንን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ዘመኑ ያፈራቸውን ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች የታጠቀና የተሟላ የሰው ኃይል ያለው አየር ኃይል መገንባት ወሳኝ ነው።
የመደመር መንግሥትም ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበና በሁለንተናዊ አቅሙ የጎለበተ ዘመናዊ አየር ኃይል ለመገንባት ያከናወናቸው ሥራዎች የሚደነቁ ናቸው።
በዚህም የአየር ኃይሉን የቴክኖሎጂ ሽግግር በማጠናከር ቀጣናዊ ሰላምን ከማስከበር ባለፈ በአህጉር ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየተሠራ ይገኛል።
በተለይም የዘመናዊ ውጊያ ስልቶችን በጥልቀት የሚረዳ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራትና የውጊያ ተልዕኮዎችን በብቃት መወጣት የሚያስችሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችንና ሌሎች ተዋጊ ጀቶችን በመታጠቅ ረገድ ትኩረት ተደርጓል።
ለዚህም አብነት የሚሆነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓመት በፊት የመረቁት ስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ ነው። ተቋሙ ለሲቪልና ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ያመርታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋሙን በመረቁበት ወቅት፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገር ውስጥ ድሮን ስለማምረት ማሰብ እንኳን የማይታሰብ ጉዳይ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በእርግጥም ዘርፈ ብዙ ተግባራትን መወጣት የሚችሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች በራስ አቅም ዲዛይን አድርጎ የማምረት አቅም መፍጠር ለኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ እመርታ ነው። ይህ አቅም የቴክኖሎጂ ነፃነትን ከማጠናከር ባለፈ የሀገሪቱን የመከላከል ብቃት ይበልጥ ለማሳደግ ያግዛል።
ቴክኖሎጂው የጠላትን እንቅስቃሴ በቅጽበት ለመከታተል፣ መረጃ ለመሰብሰብና ለመተንተን፣ እንዲሁም ፈጣንና ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። መሰል አቅሞችን ይበልጥ ማጠናከርም አየር ኃይሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የመታጠቅ ጥረቱን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና አለው።
በተጨማሪም የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚረዳ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ ዘመናዊ ትጥቆችን ለማሟላትና የውጊያ መሠረተ ልማትን ለማጠናከር ያስችላል።
አየር ኃይል ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት ጥቃቱን በአጭር ጊዜ ለመቀልበስና ኪሳራን በመቀነስ ለመጨረስ ከማስቻሉም በላይ ጠንካራ የመከላከል አቅም በመፍጠር ግጭትን ለማስቀረት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው።
የቀጣናው የጸጥታ ሁኔታ በየጊዜው በፍጥነት በሚለዋወጥበትና ግጭትን የሚፈልጉ ተዋንያን ባሉበት ሁኔታ፣ ግጭትን ሊያስቀር የሚችል የመከላከል አቅም መገንባት አስቸኳይና ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።
የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንደሚገልጹት÷ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገሪቱን የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት ለመጠበቅና ለመከላከል የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል።
አየር ኃይሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማልማትና የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በበአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ የአየር ኃይሎች አንዱ ለመሆን በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ሠራዊቱ በየቀኑ የመሣሪያ፣ የአካልና የእውቀት ፍተሻ በማካሄድ፣ የተሟላ ዲሲፕሊንና ጠንካራ ሥነ ልቦና እንዲኖረው እና ሀገሩን በብቃት እንዲጠብቅ እየተሠራ ይገኛል።
በሌላ በኩል፣ አየር ኃይሉ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በዘላቂነት ለማስቀጠል ከሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎችና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር በአቪዬሽን፣ በኤሮስፔስ ምህንድስናና በዘመናዊ ኮሙኒኬሽን ዘርፎች እየሠራ ነው። ይህም የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ አቅም ከማሳደግ ባለፈ የሰው ኃይል እውቀትና ክህሎትን ለማሳደግ ያግዛል።
በቀጣይም የጠላትን እንቅስቃሴ አስቀድሞ በመለየትና ለማክሸፍ በመዘጋጀት፣ ማንኛውንም ስጋት በብቃት ለመመከት የሚያስችል አቅም መገንባት ይጠይቃል።
ስለሆነም የጊዜውንና የነባራዊ ሁኔታውን ፍላጎት የሚመጥን ዘመናዊና በቂ አቅም ያለው አየር ኃይል የመገንባት ሥራ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል ይገባል።
Exit mobile version