Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኤርትራውያን ሀገር አልባ ያደረጋቸውን አምባገነናዊውን ሥርዓት ሊታገሉት ይገባል – የኤርትራ ሠማያዊ ማዕበል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኤርትራ ሠማያዊ ማዕበል ኤርትራውያን ሀገር አልባ ያደረጋቸውን አምባገነናዊውን ሥርዓት እንዲታገሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኤርትራ ሰማያዊ ማዕበል የዲፕሎማሲ ኃላፊ ዮኤል ዮሐንስ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ኤርትራን ከዓለም ነጥሎ የግል ርስቱ ያደረገው የኢሳያስ ሥርዓት የኤርትራውያን ዋነኛ ጠላት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለ35 ዓመታት ሀገሪቱን የግል ንብረቱ አድርጎ የያዘው የኢሳያስ አፈወርቂ አምባገነናዊ ሥርዓት ኤርትራን ምድራዊ ሲኦል አድርጓታል ያሉት ኃላፊው ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ እና ኢንቨስትመንት የሚባሉ ጉዳዮች በኤርትራውያን ዘንድ የማይታወቁ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።

በኤርትራ አንድ ዩኒቨርሲቲ ብቻ እንደነበር እና እሱም እንደተዘጋ በመጠቆም ወጣቶች የትምህርት እድል ተነፍጓቸው በግድ ወደ ውትድርና ብቻ እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኤርትራ ወጣት ሰላም ነው ሚፈልገው ያሉት ዮኤል ዮሐንስ ነገር ግን አምባገነኑ የኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ይህን አይፈልግም ነው ያሉት፡፡

የኤርትራ ወጣት የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የሥነ ልቦና ጫና እንደደረሰበት በመግለፅ የኤርትራ ወጣት ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ በዩጋንዳ እና በሌሎች አፍሪካ ሀገራት እንዲሁም ወደ አውሮፓ እየተሰደደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ኤርትራ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ቢኖሯትም ነገር ግን በአምባገነኑ አገዛዝ ምክንያት በዜጎች ስደት እና በድህነት የምትታወቅ ሀገር መሆኗን አስረድተዋል።

በመሆኑም በመላው ዓለም የሚገኙ ኤርትራውያን ሀገር አልባ ያደረጋቸውን አምባገነናዊውን ሥርዓት ለመታገል መነሳት እንደሚገባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version