አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2019 (2019) የመጀመሪያው የአፍሪካ ወታደራዊ ማርቺንግ ባንዶች ውድድርና ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ።
የውድድሩንና የፌስቲቫሉን ዝግጅት አስመልክቶ የመከላከያ ሚኒስቴር የማብሰሪያና የጋዜጣዊ መግለጫ መርሐ ግብር አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የቀድሞ የሠራዊት አባላትና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ሮዛ የሩቅነህ እንዳሉት÷ ውድድሩና ፌስቲቫሉ በሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል።
መርሐ ግብሩ በተለይም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በተለያዩ መስኮች ለማሳደግ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
አዲስ አበባ ባለፈው ዓመት ከ200 በላይ ስብሰባዎችን ማስተናገዷን አውስተው ውድድሩንና ፌስቲቫሉን በብቃት ለማስተናገድ ከተማዋ ዝግጁ መሆኗን ጠቁመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም መርሐ ግብሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ገልጸው በመርሐ ግብሩ የተሳተፉ ወታደራዊ አታሼዎችም ውድድሩና ፌስቲቫሉ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የውድድሩና የፌስቲቫሉ ሐሳብ አመንጪ የሆኑት የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል ሻለቃ ቆንሲል ተስፋዬ ወንድሙ የመርሐ ግብሩን ዓላማ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ውድድሩና ፌስቲቫሉ ወታደራዊ ማርቺንግ ባንዶች ትውፊታቸውንና ባህላቸውን ለሌሎች ሀገራት ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ሀገራት ትብብርን ለማጠናከርና በጋራ ለመሥራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ውድድሩና ፌስቲቫሉ የጎዳና ላይ ሰልፍ፣ የሜዳ ላይ ትርኢትና የልዩ ሙዚቃዎች ውድድርን የሚያካትት መሆኑም ተገልጿል።

