አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ለህዝብ የገባውን ቃል ወደ ሀግባር ለመቀየር በላቀ ቁርጠኝነት እየሠራ ነው አሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩና ካቢኔያቸው በሀረር ከተማ እየተሰሩ የሚገኙ የወንዝ ዳር፣ የተቋማት ማዕከል፣ የመንገድና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
በዚህ ወቅትም ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት÷ ለህዝቡ የገባነውን ቃል ወደ ተግባር ለመቀየርና የህዝቡን ሁለተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።
በክልሉ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጄቶች በፍጥነትና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳደሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎችም የመልካም አስተዳደር ችግር በማይፈጥር መልኩ እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የኮሪደር ልማቱ የህዝቡን የመሰረተ ልማት ተደራሽነት በተጨባጭ ከማሳደግ ባሻገር የነዋሪው የአኗኗር ዘይቤ እንዲሻሻል እያገዘ መሆኑን ጠቁመዋል።
ህዝቡም በራስ ተነሳሽነት ለፕሮጀክቶች መሳካት እያደረገ የሚገኘው ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ነው ያሉት፡፡
የኮሪደር ልማቱ በተለይም በሀረር ከተማ ስር ነቀል ለውጥ አምጥቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለመኖርና ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ የነበሩ አካባቢዎች አሁን ላይ ለህዝቡ ኑሮ የተመቹ እንዲሆኑ ማስቻሉን አመልክተዋል።
በተስፋዬ ኃይሉ

