Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ታላቁ የመደመር ስትራቴጂ፤ ለኢትዮጵያ ታላቅነት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግር የታሪክ ምዕራፎች ሲፃፉ የከረሙት፤ በግጭትና እና ለፈውን በማፍረስ ላይ በተጠመዱ ለውጦች ነበር።
እያንዳንዱ አዲስ መጣሽ ሥርዓት የቀደመውን ሙሉ በሙሉ በማፍረስ፣ የታሪክ አሻራዎችን በመደምሰስ እና ተቋማትን ከዜሮ እንዲጀምሩ በማድረግ ሀገሪቱን በፖለቲካ እና ማህበራዊ መከፋፈል ቁርሾ ውስጥ ጥሏት አልፏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) «መደመር» የተሰኘውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ፍልስፍና ይዘው ሲመጡ፣ ይህንን አጥፊ አዙሪት በማስወገድ አዲስ የመደመር፣ የመደጋገፍ እና የጋራ ዕድገት ባህልን ለማስተዋወቅ ነበር።
መደመር ማለት ያለፈውን ታሪክ ሙሉ በሙሉ መካድ ወይም ማፍረስ ማለት አይደለም።
ይልቁንም የቀደሙ አዎንታዊ ስኬቶችን በማስቀጠል፣ የነበሩ ስህተቶችን በማረም እና ለዘመኑ የሚመጥኑ አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ የተሻለች እና የበለፀገች ሀገርን የመገንባት ስትራቴጂ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ የፖለቲካ ልዩነቶች በጠላትነት እና ማንም አትራፊ ባልሆነበት በዜሮ-ሰም (Zero-sum) ጨዋታ ሲቃኙ ኖረዋል።
መደመር ይህንን ልምምድ በመቀየር ልዩነቶችን እንደ ውበት፣ ውይይትን ደግሞ እንደ መፍትሔ ይወስዳል።
ሀገርን የጠበቁ ጠንካራ ባህላዊ እና ህገ-መንግሥታዊ እሴቶች ተጠብቀው ይቆያሉ፤ ገለልተኛ እና ጠንካራ ተቋማት ለምሳሌ እንደ ፍርድ ቤት፣ የምርጫ ቦርድ እና የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን በመገንባት የህግ የበላይነትን እንዲረጋገጥ ይደረጋል፡፡
ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያቀፈ ሀገራዊ የውይይትና የምክክር መድረኮችን በመክፈት ፖለቲካዊ መረጋጋትን ማምጣት የመደመር እሳቤ ያቀፋቸው የሀገር ግንባታ መሰረቶች ናቸው።
በኢኮኖሚው ዘርፍ፤ መደመር መንግስት ብቻውን የሚያንቀሳቅሰውን የቆየ ሞዴል በመቀየር የግል ባለሀብቱን ሚና የሚያጎለብት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን እውን አድርጓል።
የፋይናንስ ዘርፉን በማዘመን፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን በማስተካከል እና የዋጋ ንረትን በመቀነስ ማክሮ- ኢኮኖሚን ማረጋጋት አስችሏል፡፡
ከግብርና በተጨማሪ በቱሪዝም፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይ.ሲ.ቲ)፣ በማዕድን እና በኢንዱስትሪ ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት በማድረግ ኢኮኖሚን እንዲሰፋ አድርጓል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የኮሪደር ልማት፣ ገበታ ለሀገር/ለትውልድ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ዳር በማድረስ የታላላቅ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እድገትን አመላክቷል።
በማህበራዊው ዘርፍ፤ መደመር የህዝቦችን አብሮነት እና መደጋገፍ የሚያጎላ ሲሆን፣ በውጭ ዲፕሎማሲ ደግሞ ዜጋን የትኩረቱ ማዕከል ያደረገ፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ የማደግ መርህን ይከተላል።
በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ቅሬታዎችን በይቅርታ፣ በውይይት እና በወንድማማችነት መንፈስ በመፍታት የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት ያጎላል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመሰረተ ልማት፣ በኃይል አቅርቦት እና በንግድ በመቀናጀት ቀጣናዊ እድገትን ያፋጥናል፤ በዚህም አህጉራዊ ትስስርን እውን ያደርጋል፡፡
ታላቁ የመደመር ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ታሪካዊ፤ ሰብዓዊ ሀብት እና የወደፊት የመበልጸግና የዘመናዊነት ትልም ለማስታረቅ የተዘረጋ ድልድይ ነው።
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version