Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጎንደር ሕዝብ ለሀገርና ለሠራዊታችን ያለው ደጀንነት ዛሬም በጽናት ይቀጥላል – አቶ ቻላቸው ዳኘው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎንደር ሕዝብ ለሀገርና ለመከላከያ ሠራዊታችን ያለው ደጀንነት ዛሬም በጽናት ይቀጥላል አሉ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው
በጎንደር ከተማ የሀገር መከላከያ ሠራዊትንና የክልሉን የጸጥታ ኃይሎች ለመደገፍ የተዘጋጀ ደማቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
አቶ ቻላቸው በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የከተማዋ ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው ያሳዩት አንድነትና ድጋፍ ለሀገርና መከላከያ ሠራዊቱ ያላቸውን ጽኑ አቋም የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ሕዝባዊ ወኔና እልህ፣ የውስጥና የውጭ ጠላቶች በሐሰተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሊያናውጡትና ሊከፋፍሉት ለሞከሩት አፍራሽ ድርጊት በአንድ ድምፅ የተሰጠ የማያወላውልና ቁርጠኝነት የተሞላበት የድል ምላሽ መሆኑን አንስተዋል።
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ዘላቂ ሰላም ለማስከበር እያሰመዘገቡት ላለው ደማቅ የድል ታሪክ ልባዊ ምስጋናና ዘላለማዊ ክብር ማቅረብ የዘወትር ተግባርንና ኩራት መሆኑን ገልጸዋል።
ሰላም ከሌለ ልማት የለም፤ ልማት ከሌለ ደግሞ ብልፅግና አይታሰብም ያሉት አቶ ቻላቸው÷ የከተማዋን አስተማማኝ ሰላም በጥብቅ ዲስፕሊን እያስጠበቅን፣ የጀመርናቸውን ታላላቅ የልማት ስኬቶችና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ጎን ለጎን በጥራትና በከፍተኛ ፍጥነት እናስቀጥላለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትና የቀይ ባሕር ፍትሐዊ የመጠቀም መብታችን በከንቱ የሚተው ወይም ታጥፎ የሚቀመጥ ሳይሆን፣ በልጆቿ ጽናት፣ እውቀትና መስዋዕትነት እውን የሚሆን ሀገራዊ ርዕይና ትውልዳዊ ግዴታ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ እስከ ቀይ ባሕር ወደብ የምናደርገውን ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስልታዊ ሽግግር በሁለንተናዊ አቅማችን በይፋ እንደግፋለን ማለታቸውንም የከተማው ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
Exit mobile version