Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሕዝቡን የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መመለስ ቀዳሚ ኃላፊነታችን ነው – አቶ ፍቅሬ አማን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝቡን የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መመለስ የአመራሩ ቀዳሚ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል አሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን፡፡
በክልሉ “ማንሰራራት ለክልላችን ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሕዝቡ በምርጫ ወቅት ድምፁን የሰጠው በመንግሥት የልማት አቅጣጫ ላይ እምነት በመጣሉ በመሆኑ የተገቡ ቃሎችን ወደ ተጨባጭ ውጤት መቀየር ይገባል።
አመራሩ ከብልሹ አሠራሮች ራሱን በማራቅ የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለበት ገልጸው፤የተደመረ አቅምን በመጠቀም በተሻለ ቅንጅትና ዝግጁነት ተግባራትን መፈጸም ይገባል ነው ያሉት፡፡
ሕዝቡን በማሳተፍ፣ ለም መሬትን፣ የማዕድን ሀብትንና የሰው ኃይልን በአግባቡ በመጠቀም የብልጽግና ራዕይን ማሳካት እንደሚገባ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
ሐሰተኛ መረጃዎችን በመታገል በሕዝቦች መካከል መተማመንን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው፤ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም በመገንባትና ቴክኖሎጂን በማስፋት አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
Exit mobile version