አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገሩን ለመጠበቅ የወሰደው ርምጃ የሚበረታታ ነው አሉ የተለያዩ ሀገራት አታሼዎች፡፡
ለተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼ አባላት በቢሾፍቱ አየር ኃይል በኢትዮጵያ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በአፍሪካ ህብረት የእንግሊዝ የመከላከያ አታሼ ሌተና ኮሎኔል ጋሪ ዎልፌንደን ያደረጉት ጉብኝት ባለፉት ሶስት ሳምንታት ምን እንደተካሄደ በግልጽ ያየንበት ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገሩን ለመጠበቅ የወሰደው ርምጃ የሚበረታታ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት እና በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ የመከላከያ አታሼ እና የመከላከያ አታሼዎች ማህበር ምክትል ዲን ኮሎኔል ካረን ሳች በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገሩ ድንበር መከበር የወሰደው ርምጃ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
ህገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ጦርነቱን ከጀመረ በኋላ ከኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ከመከላከያ ሚኒስቴር ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ይጠብቁ እንደነበር ጠቁመው፤ ዛሬ ይህ ገለጻ መደረጉ ስለ ሁኔታው ያለንን ግንዛቤ ለማስተካከል አግዞናል ያሉት ደግሞ የባንግላዴሽ የመከላከያ አታሼ ብርጋዴል ጄኔራል ሸሪፉል ኢስላም ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ሁሉንም ዓለም አቀፍ ህጎች እና ደንቦች እየጠበቀ እንደሆነ በመመልከታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የኬንያ የመከላከያ አታሼ ብሪጋዴር ጄኔራል ሮባ ዋሪዮ በበኩላቸው፤ እንደ የመከላከያ አታሼ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት ይህንን እድል በማግኘታችን ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡
ድንበር ተጋሪ ሀገራት እንደመሆናችን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ህግን ተከትሎ የወሰደውን ርምጃ እንገነዘባለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የጋቦን የመከላከያ አታሼ ኮሎኔል አሪስቲድ አንጊሌት በበኩላቸው፤ የሠራዊቱ እና የመከላከያ ኃይሎች ዋነኛ ግዴታ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት መጠበቅ እንዲሁም በሀገራቸው ውስጥ ላሉ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ዜጎች ደህንነትን ማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡
የተደረገው ገለጻ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጨውን ሀሰተኛ መረጃ ለማጥራት እና የኢትዮጵያን ትክክለኛ አቋም ለመረዳት እንዳገዛቸው አብራርተዋል፡፡
በእመቤት ሲሳይ

