Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመላው አፍሪካ ሃብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብጽ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የመላው አፍሪካ ሃብት አድርጋ መቀበል ይገባታል አሉ ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊ የፖለቲካ ሳይንቲስትና ጠበቃ አለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር)፡፡
በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሳን በርናርዲኖ መምህር የነበሩት አለማየሁ (ፕ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን የማልማት መብቷ በዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ እና በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ባለው የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ መታየት አለበት፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመላው የአፍሪካ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፤ የዓባይ ውሃን አስመልክቶ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ውስጥ ኢትዮጵያ እንዳልነበረች አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችባቸው ውሎች ልትገደድ እንደማትችል አስገንዝበዋል።
ግብጽ የዓባይ ተፋሰስን የተቀየረ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ ሁኔታዎችን መገንዘብ እንዳለባት ገልጸዋል፡፡
የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አክትሟል፤ ግብፅም በዓባይ ላይ የቅኝ ግዛት ባለቤትነት መብት አለኝ ልትል አትችልም ያሉ ሲሆን፤ የታሪክ ጥያቄዎች የኢትዮጵያን የልማት ምኞት ለመገደብ መሠረት መሆን እንደሌለባቸው አብራርተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዋናነት ኤሌክትሪክ ለማመንጨትና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለመደገፍ ታስቦ የተገነባ ትልቅ ኢንቨስትመንት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ግድቡ ለቀጣናው የኢኮኖሚ እድገት ሊያበረክተው በሚችለው አስተዋጽኦ መታየት እንዳለበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከውሃ ኃይል የምታመነጨው ኤሌክትሪክ ለኢንዱስትሪ፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለግብርና ልማት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራን አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ለጂቡቲ እና ለታንዛኒያ የምታደርገውን የኤሌክትሪክ ሽያጭ የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር የኃይል መሠረተ ልማት ያለውን አቅም የሚያሳዩ ማረጋገጫዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
የቀጣናው የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት እና የልማት እንቅስቃሴ ካደገ ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ውስጥ ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ሊፈጥር እንደሚችል አብራርተዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ሀብት ነው ያሉ ሲሆን፤ የፕሮጀክቱ አስፈላጊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ወሰን በላይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ግብፅ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያሏት ስጋቶች በውይይት እና የተፋሰሱ ሀገራትን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ በስምምነት መፍታት ትችላለች ብለዋል።
ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚመነጨው ኤሌክትሪክ ኃይል የቀጣናውን ልማት ለማፋጠን ያገለግላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የግብፅ መሪዎች የኢኮኖሚ ትስስርን ከመደገፍ ይልቅ ኢትዮጵያን ለማወክ ያለመ ፖሊሲ እየተከተሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግብፅ የተሳሳተ ፖሊሲ ከመከተል በመላው ቀጣናው ለጋራ ብልጽግና ከኢትዮጵያ ጋር የኢኮኖሚ ትብብር ማድረጉ አዋጪ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያን በወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ጫና ለማዳከም የሚደረጉ ሙከራዎች እንደማይሳኩም ገልጸዋል።
ግብፅ አካሄዷን በመመርመር ሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ የሚጠቅሙ የልማትና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን መከተል እንደሚገባት ተናግረዋል።
Exit mobile version